Back

የኤርትራ ልዑክ ወደ አማራ ክልል ሊመጣ ነው

ነሐሴ 11፣2010

በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተመራ የኤርትራ ልዑካን ቡድን  ወደ አማራ ክልል ሊመጣ ነው፡፡

ከሁለት ቀን በፊት ወደ አስመራ ያቀናው የአማራ ክልል ልዑክ ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ሀይል ንቅናቄ  ጋር ከደረሰው ስምምነት በተጨማሪ ከኤርትራ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋርም ውይይት መደረጉን የልዑኩ አባልና የአማራ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁን በፌስ ቡክ ገፃቸው አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ክልል ልዑክ በኤርትራ በነበረው ቆይታ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ልዩ አማካሪ አቶ የማነ ገብረአብ ጋር የኤርትራ እና የኢትዮጵያዊውያንን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ  ውይይት ማድረጉንም አቶ ንጉሱ ተናግረዋል፡፡

በዚህም በቅርቡ በአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሚመራ የልዑካን ቡድን ወደ አስመራ እንዲጓዝ ከስምምነት የተደረሰ ሲሆን ፣ በአፀፋው  ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመሩት የልዑካን ቡድን ወደ አማራ ክልል እንዲመጣም ከስምምነት መደረሱን ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

በአማራ ብሔራዊ ክልል በተለይም በጎንደር እና በባህር ዳር በርካታ ኤርትራውያን እንደሚኖሩም ተመልክቷል፡፡

የአማራ ክልላዊ መንግስት በቀጣዩ 2011 ዓመት  ከአጎራባች ክልሎች ጋርም ጠንካራና ተከታታይ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በማካሄድ አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር እንደሚሰራም አያይዘው ገልፀዋል፡፡