Back

በአዲስ አበባ በትምህርት ቤቶች የተከሰተ የመፅሃፍ እጥረትን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን የአስተዳደሩ ት/ቢሮ አስታወቀ

ጥቅምት 12፣2011

በአዲስ አበባ በመንግስትና በግል ትምህርት ቤቶች የተከሰተው የመፅሃፍ እጥረት በቅርቡ እንደሚፈታ የከተማ አስተዳደሩ  የትምህርት ቢሮ አስታወቀ᎓᎓

የትምህርት ቢሮው የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አበበ ቸርነት  ለኢቢሲ እንደገለፁት በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የመንግስትና የግል ትምህር ቤቶች የሚታየው የመፅሃፍ እጥረት በአጭር ጊዜ ይፈታል፡፡

ለዚህም የትምህርት ቢሮው በአንድ የማተሚያ ድርጅት አማካኝነት ከ2.7 ሚሊዮን በላይ መፅሃፍትን እያሳተመ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ ህትመቱ እንደተጠናቀቀ   ወዲያውኑ ወደ የትምህርት ቤቶቹ በማሰራጨት እጥረቱ እንደሚቀረፍም አቶ አበበ ገልፀዋል᎓᎓

በአዲስ አበባ ከተማ የመንግስትም ይሁን የግል ትምህርት  ቤቶች መፅሃፍ የሚያገኙት ለከተማ አስተዳደሩ ትምህር ቢሮ  ቀደም ብለው በሚልኩት ፍላጎት የሚሰራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከህትመት በኃላ ግን ወደ ስርጭት ሲገባ እጥረት መፈጠሩን ቢሮው ገልጿል፡፡

በህትመት ውስንነት ምክንያት የተፈጠረውን የመፅሃፍት እጥረት ለመቅረፍም  በፍጥነት ወደ መፍትሄ መገባቱን ኃላፊው አመልክተዋል፡፡

የመፅሃፍ እጥረት አለ እየተባለ  በአንዳንድ ቦታዎች በጥቁር ገበያ ሲሸጥ መታቱ ከየት የመጣ ነው ተብለው ሲጠየቁ ኃላፊው፣ ጉዳዩ በደንብ ጥናት ማድረግ ይጠይቃል ብለዋል፡፡ ቢሆንም ቢሮው ለክልሎችም መፅሃፍትን  ስለሚያሰራጭ እየተሸጡ ነው የተባሉ መፅሃፍት ከክልሎች ሊመጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡፣

ከዚህ ባለፈም ባለፈው አመት ተማሪዎችን አስተምረው በዚህ አመት ትምህርት ቤቶቻቸውን ከዘጉ አካላት፣ እንዲሁም የግል ትምህርት ቤቶች  ከቢሮው በወሰዱት መፅሃፍት ልክ ተማሪ ሳይኖራቸው ሲቀር  ትርፍ መፅሃፍትን ወደ ገበያ ሊያወጡ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል᎓᎓

የመፅሃፍት እጥረት በትምህርት ቤቶች እያለ በጥቁር ገበያ የመገኘታቸው ምክንያት ብዙ ቢሆንም ቢሮው  በማጣራት ስራ የችግሩን ምንጭ ለመለየት እየሰራ መሆኑን አመልክቷል፡፡

በመስፍን ገ/ማርያም