Back

የመከላከያ ኃይሉ የተፈናቀሉ ዜጎችን ሰላም በማረጋገጥ ወደየአካባቢያቸው እንዲመለሱ እያደረገ መሆኑን ገለፀ

ታህሳስ 30፣2011

በተለያዩ አካባቢዎች በብሔር ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ሰላም በማረጋገጥ ወደየአካባቢያቸው እንዲመለሱ እየሰራ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

ሚኒስቴሩ ያለፈውን ግማሽ የበጀት ዓመቱን የስራ አፈፃፀም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡

ሚኒስትሯ ኢንጂነር አዒሻ ሙሐመድ እንደገለፁት የመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ማሻሻያ በማድረግ የተለያዩ የአደረጃጀት ለውጦች መጥተዋል፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት ያለነበረውን የባህር ኃይል ተቋቁሞ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ስር እንዲደራጅ የሚያስችል ስራ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስቴር የአዋጅ ማሻሻያ ከማድረግ ጀምሮ የመከላከያ ሰራዊት አባላት አደረጃጀት የሁሉም ብሔር ውክልና እንዲኖረው ተደርጎ መዋቀሩንም ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ሲመልሱ ሚንስትሩ ገልጸውል፡፡

በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በጎሳ ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ሰላም በማረጋገጥ ወደየአካባቢያቸው እንዲመለሱ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም በሪፖርቱ ላይ ቀርቧል፡፡

መከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጅነር አዒሻ በአሀዝ አስደግፈው ባይገልፁም  ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርንና በህገወጥ መልኩ ወደ ውጭ ሊወጡ የነበሩ ሰዎችንም ከክልል የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉንም አስረድተዋል፡፡

በቀጣይም፣ መከላከያ ሚኒስቴር በአገሪቱ የያዛቸውን ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ንብረቴ ተሆነ