Back

ከነባር የኦነግ አመራሮች ጋር አብረን መስራት ፍላጎታችን ነው- አቶ ለማ መገርሳ

ጥር 2፡ 2011 ዓ.ም

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ከነባር የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራር ገላሳ ዲልቦና ቡድናቸው ጋር ዛሬ ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ላይ አቶ ለማ በገላሳ ዲልቦ የሚመራው ኦነግ ጥሪያቸውን አክብሮ ወደ አገር ቤት በመግባቱ ምስጋና አቅርበው፣ ከእነሱ ጋር አብረው ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

ከውጭ የገቡ የፖለቲካ ሃይሎች የአገሪቱን ህግ አክብረው የሚሰሩ እንዳሉ ሁሉ ከሰላም ተጻራሪ ሆነው እየሰሩ የሚገኙ እንዳሉም ገልጸዋል አቶ ለማ፡፡

የኦነግ ነባር አመራር የሆኑት አቶ ገላሳ ዲልቦ በበኩላቸው እኛ ወደ አገር ቤት የገባነው በተደረገልን ግብዣ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታን አይተን ነው፣ የመጣነውም ከእናንተ ጋር አብረን ለመታገል ነው ብለዋል፡፡

በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን ያጡበትን ትግል ወደ ኋላ እንዲመለስ የማንፈልግ በመሆኑ ለውጡ ወደ ፊት እንዲጓዝ እንሰራለን ያሉት አቶ ገላሳ፣ እኛ ያለን ረጅም የትግል ልምድ በመሆኑ ልምዳችንን እናካፍላችኋለን፣ ፊት ለፊት ተነጋግረን አብረን እንሰራለንም ብለዋል፡፡

በኦላና ያዴሳ