Back

ባለፉት 6 ወራት የወጭ ንግድ ገቢ ዝቅተኛ አፈፃፀም ማስመዝገቡ ተገለፀ

ጥር 28፣2011

ባለፉት በስድስት ወራት የአገሪቱ የወጭ ንግድ ገቢ ዝቅተኛ አፈፃፀም ማስመዝገቡን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት በወጭ ንግድ ገቢ አገሪቱ 1 ነጥብ 21 ቢሊዮን ዶላር እንዳገኘች በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የወጪ ንግድ ማስፋፊያ ጀነራል ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ሙሉጌታ በተለይ ለኢቢሲ ተናግረዋል፡፡

ይህም ከተቀመጠው እቅድ አኳያ 62 በመቶ አፈፃፀም ሲያስመዘግብ፣ አምና ከነበረው ገቢ አንፃር ደግሞ የ10 በመቶ ጉድለት ማሳየቱን ገልፀዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት አነስተኛ ገቢ ከሚያስገኙ የተወሰኑ ምርቶች ወጪ አብዛኛው ምርቶች ከታቀደላቸው በታች አፈፃፀም አሳይተዋል ብለዋል አቶ አሰፋ፡፡

በወጭ ንግድ ገቢ ትልቅ ድርሻ ያላቸው እንደ ቡና፣ጥራጥሬና የቅባት እህሎች አነስተኛ  የገቢ አፈፃፀም እንዳስመዘገቡም ጠቅሰዋል፡፡

ለአፈፃፀሙ ዝቅተኛ መሆን በአለም ገበያ የምርቶቹ ዋጋ በመውረዱና በአገር ውስጥ የፀጥታ መደፍረስ ችግር በመከሰቱ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በተለይም በስድስት ወራት ውስጥ የቡና ምርት ገቢ አፈፃፀም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር የ12 ነጥብ 54 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

ልክ እንደቡና ሁሉ በወጭ ንግድ ገቢ ግኝት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው የጥራጥሬና የቅባት እህሎች የወጭ ገቢ አፈፃፀማቸው አነስተኛ ነው፡፡

በአንፃሩ ባለፉት ስድስት ወራት በወጭ ንግድ ገቢ አነስተኛ ድርሻ ያላቸው እንደጫት፣ ኤሌክትሪክና ታንታለም ያሉ ምርቶች የተሻለ አፈፃፀም አስመዝግበዋል፡፡

በተለይ በመንፈቅ ዓመቱ የጫት ምርት የእቅድ ክንውኑን 103 በመቶ በማሳካት ከፍተኛ አፈፃፀም አሳይቷል ነው የተባለው፡፡

በቀጣይ የአገሪቱን የወጭ ንግድ ገቢ ለማሳደግ ወደ ውጭ አገራት የሚላኩ የአምራች ኢንዱስትሪንና የግብርና ምርቶችን አቅርቦት መጨመር እንደሚያስፈልግም ተነግሯል፡፡

ከዚህም ባሻገር በግብርና ምርቶች የግብይት ሰንሰለት የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት ብሎም የአገሪቱን የውጭ ንግድ ገቢ የሚያሳንሱ ኮንትሮባንድ ንግዶችን ለመከላከል ከክልል አካላት ጋር የተቀናጀ ስራ እንደሚጠይቅም ሚኒስቴሩ ተገንዝቧል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ የሚገኘውን የአገሪቱን የውጭ ንግድ ገቢ ለማሳደግ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጠይቋል፡፡

ሪፖርተር፦ ሰለሞን አብርሃ