Back

በማደግ ላይ ባሉ ክልሎችና አርብቶ አደር አካባቢዎች ዘላቂ ሠላም ለማስፈን እንደሚሠራ የሠላም ሚኒስቴር አስታወቀ

የካቲት 13/ 2011

በማደግ ላይ ባሉ ክልሎችና አርብቶ አደር አካባቢዎች ዘላቂ ሠላም ለማስፈን እና ህብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራ የሠላም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ዘርፍ አፈፃፀምና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ከተማ ዉይይት አካሄዷል፡፡

በሚኒስቴሩ የፌዴራሊዝም እና ተመጣጣኝ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ስዩም መስፍን የተመራው ልዑክ በክልሉ የመስክ ምልከታ ያደረገ ሲሆን ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት አካሂዷል።

በዉይይቱም ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ክልሎች የሚደረገው ድጋፍ ውስንነት እንደነበረበት ተነስቷል።

በተለይ በመንደር ለተሰባሰቡ የህብረተሰብ ክፍሎች በሁለንተናዊ ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ ድጋፍ የሚደረገዉ በጀት በያመቱ እየቀነሰ መምጣቱ ተጠቁሟል፡፡

በሠላም ሚኒስቴር የፌዴራሊዝም እና ተመጣጣኝ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ስዩም መስፍን እንደተናገሩት በክልሉ ዘላቂ ሠላም እንዲረጋገጥና ህብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚ ለማድረግ የ10 ዓመት ፍኖት-ካርታ ተዘጋጅቷል፡፡

በፌደራል ልዩ ድጋፍ የሚከናወኑ ፕሮጄክቶች ለታለመላቸዉ ዓላማ መዋላቸዉን የሚከታተል የፕሮጄክት ፅ/ቤት በክልሉ እንዲቋቋም የቀረበዉን ምክረ ሃሳብ የከልሉ መንግስት ተቀብሎታል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው የሠላም ሚኒስቴር በክልሉ ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ እና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተቀመጡ ዕቅዶችን ውጤታማ ለማድረግ የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል መደረግ አለበት ብለዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ያለለት ወንድዬ (ከአሶሳ)