Back

ኤች ኤይ ቪ ኤዲስን መከላከል ስኬታማ ያደርጋል የተባለለት የኮንዶም ስታራቴጂ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ ሊገባ ነው

መጋቢት 24፣2011

ኤች ኤይ ቪ ኤዲስን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ስኬታማ ለማድረግ የኮንዶም ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ ሊገባ መሆኑን የፌዴራል  ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

ኤች አይ ቪ ኤዲስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የዜጎች ቸልተኝነት እንዳሳሰበው ጽ/ቤቱ ገልጿል፡፡

የጽ/ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር  አቶ ዳንኤል በትሪ ለኢቲቪ እንደተናገሩት ቸልተኝነቱ ለቫይረሱ መስፋፋት በር እየከፈተ ነው፡፡  

በመሆኑም የፌዴራል  ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት በቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የኮንዶም አቅርቦትን ውጤታማ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በዚህ በጀት ዓመቱ የኮንዶም ስትራቴጂ ተዘጋጀቶ ወደ ስራ ለማስገባት ጽ/ቤቱ ዝግጀት ላይ መሆኑን የህዝብ ግንኘነት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡  

በሆቴሎችና መዝናኛ ማዕከላት ነፃ የኮንዶም ስርጭት ቀንሷል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም አቶ ዳንኤል ሲመልሱ ክፍተቱ የሚፈጠረው  እንደ ጤና ሚኒስቴር፣የመደሃኒት ግዢና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሚፈጥሩት የቅንጅት ውስንነት ነው ብለዋል፡፡

ይሁንእንጂ ጤና ጣቢያዎችን ጨምሮ ኮንዶም በነፃ እንደሚሰራጭም ገልፀዋል፡፡

የፌዴራል የኤች አይ ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት (HAPCO) ሀብትን በማሰባሰብ ኮንዶምና የምርመራ ቁሶች(test kit) እንዲሁም ተመሳሳይ ቁሳቁሶችን በመግዛት የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማዘጋጀት ሚናውን እየተወጣ መሆኑን አመልክቷል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአገር ደረጃ 649 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ኤች አይ ቪ ኤድስ በደማቸው የሚገኝ ሲሆን አገራዊ የስርጭት ምጣኔውም 0.96 እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በአለም ጤና ድርጅት መረጃ መሰረት አንድ አገር በኤች ኤይ ቪ ኤድስ ወረርሽን ውስጥ ነች የሚባለው የስርጭት ምጣኔው 1 በመቶና ከዚያ በላይ ሲሆን ነው፡፡

በአበባየሁ ከፈኒ