Back

ኮትሮባንድና የመንግስት መዋቅር ውስንነት የማዕድን ዘርፉ ፈተናዎች መሆናቸው ተገለጸ

ሚያዝያ 20፣2011

የመንግስት መዋቅር ውስንነትና ህገ ወጥ የማዕድናት ግብይት ለዘርፉ አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆን ተግዳሮት መሆናቸውን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ለአገሪቱ የማዕድናት የውጭ ገበያ ድርሻ በተለይ በዘንድሮው ዓመት  ዝቅተኛ አፈፃፀም አሳይቷል፡፡

ኮንትሮባንድ፣ ዘመናዊ የግብይት ስርዓት እና የመንግስት መዋቅር አለመኖር ዋነኛ የማዕድን የውጭ ገበያ ድርሻ ማነስ ምክንያቶች መሆናቸውን በሚኒስቴሩ ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት አቶ ኪሮስ አለማየሁ ለኢቲቪ ገልጸዋል፡፡

የማዕድን የማምረት ስራ በአገሪቱ ጥጋጥግና መሰረተ ልማት ባልተሟላባቸው አካባቢዎች የሚካሄድ በመሆኑ ዘርፉ ለኮትሮባንድና ሌሎች ችግሮች መጋለጡን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

የማዕድን አምራቾችና ተቀባይ የሆነውን ብሔራዊ ባንክ ቀጥታ የሚያገናኝ ዘመናዊ የግብይት ስርዓት አመለኖርም እንደ ችግር ተገልጿል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የመንግስት የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ ልክ እንደሌሎቹ ፣ የማዕድን ዘርፍ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ደረጃ ራሱን ችሎ የተዋቀረ አለመሆኑ ዘረፉን ትኩረት እንዳያገኝ አድርጎታል፡፡

በመሆኑም ከዘርፉ የሚገኘውን አበርክቶ ለማሻሻል በጥናት ላይ የተመረኮዘ  እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡

በዚህም ዘርፉ በዞንና በወረዳ ደረጃ ራሱን ችሎ እንዲቋቋምና መዋቅሩ ለስልጠና፣ ለድጋፍና ለቁጥጥር እንዲመች ለማድረግ እየተሰራ ነው ብሏል፡፡

በተለይ ኦፓልን ጨምሮ እንደ ወርቅ፣ ኤሜራልድ፣ ሳፋዬር የመሳሰሉና ለኮትሮባንድ የተጋለጡ ማዕድናትን ወደ ዘመናዊ ግብይት ስርዓት ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ሚኒስቴር አመልክቷል፡፡

በዮሴፍ ለገሰ