Back

በስራ ላይ ያለው የጋራ ገቢ አስተዳደርና ማከፋፋያ ቀመር የግልጽነትና የፍትሃዊነት ችግር እንዳለበት ተጠቆመ

ሚያዝያ 26፣2011

በ1989 በፌዴሬሽን ምክር ቤት የወጣው ቀመሩ ላለፉት 22 አመታት አንዳችም ማሻሻያ ሳይደረግበት አሁንም ስራ ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

ስራ ላይ ያለው ቀመር ወቅታዊ ሃገራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ለማስገባት ካለማስቻሉም ባሻገር ፍትሃዊ የገቢ አስተዳደርና የገቢ ክፍፍልን በፌዴራልና በክልል መንግስታት መካከል ለመፍጠር አለማስቻሉን የቀረበው የክለሳ ጥናት የመጀመሪያ ረቂቅ ሰነድ አመልክቷል።

ችግሩ በፌዴራል መንግስት በተጣለባቸው ከፍተኛ የወጪ ኃላፊነት ሳቢያ የበጀት ድጋፍ ጥገኛ በሆኑት የክልል መንግስታት ዘንድ ቅሬታን ከመፍጠሩም በላይ እኩል የመልማትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ መሆኑ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 98 የተሰጠውን «የጋራ የታክስና የግብር» ስልጣን በመረመረው የማሻሻያ ሰነድ ላይ ተገልጧል።

የችግሩ አሳሳቢነት በተገለፀበት ሰነድም የተሻለ ልምድ ካላቸው ሃገራት የተቀመረ እና ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስችል የማሻሻያ ምክረ ሃሳብ ቀርቧል።

በምክረ ሃሳቡ መሰረትም 
ከጋራ ገቢ አስተዳደር አንፃር፦
1. በርካታ ቅርንጫፍ ያሏቸው መስሪያ ቤቶች በዋና መስሪያ ቤታቸው በኩል ግብር እንዲከፍሉና እንዲከፋፈል፣
2. ሙሉ ስራው በአንድ ክልል ሆኖ ዋና መ/ቤቱ አዲስ አበባ ከሆነ ተቋም የሚሰበሰብ ገቢን የፌዴራሉና የክልሉ መንግስታት እንዲከፋፈሉ፣
3. ሙሉ ስራው በአንድ ክልል ሆኖ ዋና መ/ቤቱ ሌላ ክልል ለሆነ ተቋም የፌዴራል መንግስቱ ድርሻ ተነስቶ ቀሪውን ክልሎች እንዲከፋፈሉ፣
4. ተቋማት የሚከፍሉትን የግብር መጠን መከታተያ ጠንካራ ስርዓት እንዲዘረጋ 
5. ጠንካራ የሪፖርት ስርዓት እንዲፈጠርና የበይነ መንግስታት ግንኙነት እንዲጠናከር የሚል ሲሆን

ከጋራ ገቢ ክፍፍል አንፃር ደግሞ 
1. የስራ ገቢ ግብር ለክልሎች ቢሰጥ፣
2. ከንግድ ትርፍ ግብርና ከባለ አክሲዮኖች ትርፍ ገቢ ግብር ጋር በተያያዘ ክልሎች የሚያገኙት ገቢ ከበጀት ድጎማና ድጋፍ ውስጥ ባይካተት 
3. የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) እና ኤክሳይዝ ታክስን በተመለከተ ለመከፋፈል ምንም ዓይነት ምክንያት የሌለው በመሆኑ በእኩል ቢከፋፈል፣
4. ከተፈጥሮ ሃብት የሚሰበሰብ የሮያሊቲ ገቢ የሁሉም በመሆኑ ለሁሉም እኩል በነፍስ ወከፍ መከፋፈሉ ቢበጅም የአካባቢው ማ/ሰብ ከተፈጥሮ ሃብቱ ጋር ያለውን ባህላዊና ታሪካዊ የባለቤትነት ስሜት የተሻለ ትኩረት ለመስጠት ሲባል ገቢውን ለፌዴራል፣የገቢ ምንጩ ለሚገኝበት ክልል፣ለአካባቢው አስተዳደርና እና ለሌሎች የሃገሪቱ ክልሎች ጭምር ማከፋፈሉ ተገቢ ነው የሚል ሃሳብ ቀርቧል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በቀረበው ረቂቅ የማሻሻያ ሰነድ ላይ በከፍተኛ የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት እና በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ውይይት እየተደረገበት ነው።

በአልዓዛር ተረፈ