Back

የደቡብ ክልል የጤና ባለሙያዎች ያነሷቸው ጥያቄዎች በመንግስት በኩል ተቀባይነት አግኝተዋል

ግንቦት 06፣2011

የደቡብ ክልል የጤና ባለሙያዎች ላነሷቸው ጥያቄዎች መለስ መስጠት ዓላማ ያደረገ ውይይት ዛሬ በሃዋሳ ተካዷል፡፡

ዉይይቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የጤና ባለሙያዎች ላነሷቸው ጥያዌች በክልሉ ደረጃ መፍትሄ ለማፈላለግ ያለመ ነበር፡፡ 

በዉይይቱ የተሳተፉት የጤና  ሚኒስሩ ዶ/ር አሚር አማን ከባለሙያዎቹ ጋር በሚከተሉት ጉዳዮች ከመግባባት መድረሳቸዉን በፌስ ቡክ ገፃቸው ገልፀዋል፡፡

በክልሉ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት አንፃር ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ  ለሁሉም የጤና ባለሙያዎች ተጨማሪ የስራ መደብ ለመክፈት የሚያስችል በጀት ለመያዝ ስምምነት ላይ ተደርሷል::

ከግንቦት 2011 ጀምሮ የትርፍ ሰዓት እና የጥቅማጥቅም ክፍያ ላይ የሚቆረጠውን ግብር ተመጣጣኝ ክፍያ በክልሉ መንግስት እና በየደረጃው ባለው የአስተዳደር እርከን እንዲሸፈን ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ከዚህ በፊት ወደ ጎን የነበረውን ሙያዊ እድገት ከግንቦት 2011 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ላይ እንዲሆንም ይደረጋል ተብሏል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የጤና ባለሞያዎች ጥቅማጥቅም ክፍያዎች ወጥ እንዲሆኑ በ2005  የወጣው የጥቅማ ጥቅም መመሪያ በደቡብ ክልል የጤና ተቋማት እስከ ጤና ጣቢያ ድረስ ከግንቦት 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆንም ስምምነት ላይ ተደርሷል ።

በመመሪያው ላይ ያልተካተቱ የሙያ ዘርፎች የተጋላጭነት ክፍያ በአጭር ጊዜ እንዲካተት ይደረጋልም ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ደመወዝ በክልሉ በሚገኙ በሁሉም አካባቢዎች ከግንቦት 2011 ዓ.ም ጀምሮ ወጥ እንዲሆን መወሰኑንም ዶ/ር አሚር አስታውቀዋል፡፡

ቀሪ ያልተፈቱ ችግሮችን ለመፍታት በፌደራል ደረጃ ከተቋቋመው ግብረ ሀይል ጋር በቅርብት በመስራት በክልሉ ተፈፃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል ተብሏል፡፡