Back

በቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ መስመሮች በሚገቡ በዕድ ነገሮች የማጣራት ሂደቱን እያስተጓጎሉ መሆኑ ተገለጸ

በአዲስ አበባ የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ወደ ፍሳሽ መስመሮች በሚገቡ ቤንዚን፣ ናፍጣ፣ የሞተር ዜይት፣ ኬሚካል፣ ቅባቶች፣ የዝናብ እና የጎርፍ ውሃ እንዲሁም በቤት ውስጥ ፍሳሽ ምክንያት ማጣሪያ ጣቢያው ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት ነው ተባለ፡፡

 

በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅና የፍሳሽ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ተስፋዬ አለም ባዩ በፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች ዙሪያ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

 

ሃላፊው እንዳሉት የማጣሪያ ጣቢያው የተለያዩ ክፍሎች ላይ እንዲሁም በባዮሎጂካል የማጣሪያ ክፍል ላይ ጉዳት በማድረሱ የማጣራት ሂደቱን እያስተጓጎለ ነው፡፡

 

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ የተገነባው የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ በተመሳሳይ መልኩ እንደጸጉር፣ ጨርቃጨርቅ፣ አጥንት እና ጠጣር ነገሮች እና የተለያዩ ላስቲኮች እየገቡ ጉዳት እያደረሱ ናቸው ብለዋል፡፡

 

ከኢንዱስትሪ፣ ከጋራጅ እና ከተለያዩ መኖሪያ ቤቶች የሚወጡ ፍሳሾች በማጣራት ሂደቱ ላይ ችግር እየፈጠሩ በመሆኑ ህብረተሰቡና ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

 

ወደ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያው መላክ ያለባቸው የመጸዳጀ ቤት ፍሳሽ ብቻ በመሆናቸው ተጨማሪ ባዕድ ነገሮች እንዳይገቡ ሃላፊው ጥሪ አድርገዋል፡፡

የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች ላይ የሚከደኑ የብረት ክዳኖች በተለያየ ምክንያት ይሰረቃሉ ያሉት ኃላፊው፣ የዝናብ ዉሃና ጎርፉ እየገባ የማጣራት ሂደቱን በማሰተጓጎል ላይ ይገኛል፡፡

ህብረተሰቡ የፍሳሽ ማስወገጃ ኪዳኖችን የሚሰርቁ ወይም ጉዳት የሚያደርሱ አካላትን ካየ ለተቋሙ እንዲያሳውቅ ጠይቀዋል፡፡

በብሩክ ተሰፋዬ