Back

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ለሌሎች አገራት አርአያ በሚሆን መልኩ ለማደራጀት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

ሐምሌ 2 ቀን 2011 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ለሌሎች አገራት አርአያ በሚሆን መልኩ ለማደራጀት እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ተናገሩ፡፡

አስተዳደሩ ለከተማው የፖሊስ አባላት የምስጋና ስነ ስርዓት አካሂዷል፡፡

በሸራተን አዲስ በተካሄደው ስነ ስርዓት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው የከተማይቱን ሰላም የተረጋጋ ለማድረግ ፖሊስ ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ የረቀቁ የወንጀል ድርጊቶችን ተከታትሎ አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ የሚደነቁ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛልም ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው ለከተማው ሰላም መጎልበት የፖሊስ አባላት እያደረጉት ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

የፖሊስ አባላቱ የበለጠ ተነቃቅተው በወንጀል መከላከሉ ስራ የተሻለ ውጤት ያስመዘግቡ ዘንድ እንዲሟሉላቸው የጠየቋቸው ጥያቄዎች ተቀባይነት አግኝተው በካቢኔው መፅደቃቸውንም ገልፀዋል፡፡

ጥያቄዎቹ በቅርቡ ምላሽ ማግኘት እንደሚጀምሩና የፖሊስ አባላቱ የደንብ ልብስም እንደሚወየር ምክትል ከንቲባው ቃል ገብተዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለኢቲቪ የሰጡ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላትም ቃል በተገባላቸው ጉዳይ መደሰታቸውንና በቀጣይ ስራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ጥላሁን ካሳ