Back

በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ከጥር 24 ጀምሮ በተቀሰቀሰ ግጭት የህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት እየደረሰ ነው

የካቲት 1፣2011

በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ከጥር 24 ጀምሮ በተቀሰቀሰ ግጭት ለበርካታ ሰዎች ሞትና ለንብረት ውድመት ምክንያት መሆኑን የአማራ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ፡፡

በተለይ የ24ኛ ክፍለ ጦር በ33ኛ ክፍለ ጦር በሚተካበት ወቅት በአካባቢው የተሰማሩ ፅንፈኛ ኃይሎች አጋጣሚውን በመጠቀም ባስነሱት ግጭት ከበርካታ ሰዎች ሞት በተጨመሪ ቤቶችም ተቃጥለዋል ብሏል ክልሉ፡፡በዚም የተነሳ ቀላል የማይበል ቁጥር ያለው የአካባው ነዋሪ ከቀየው መፈናቀሉን የአማራ ክልላዊ መንግስት የመንግሰት ኮሙኒኬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማኻኝ አስረስ በተለይ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡

ከጎንደር ወደ አርማጭኾ የሚወስደው ምስራቅ  ደንቢያ የትራስፖርት ሂደቱ እየተስተጓጎለ  መሆኑንና በዛሬው ዕለት በአካባቢው ሰርገው የገቡ ፅንፈኛ ኃይሎቹ ሰዎችን ጠልፈው እሰከመውሰድ መድረሳቸውንም  አቶ አሰማኻኝ ተናግረዋል፡፡

በየቀኑ እየደረሰ ያለው ጥፋት የአደጋውን መጠንና የደረሰውን ጉዳት ለማወቅ አስቸጋሪ እንዳደረገውም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው ለደረሰው  ዝርፊያና ወንጀሎች ቡድኖቹ በተደራጀ ሁኔታ መፈፀማቸውንም ክልሉ ገልጿል፡፡

በክልሉ ከተመዘገበው 80ሺህ ተፈናቃይ ውስጥ 39ሺህ ያህሉ ከዚህ ቀደም በማዕከላዊ ጎንደር  በተፈጠረ ግጭት ቀያቸውን ጥለው የተሰደዱ ናቸው፡፡

የክልሉ መንግስት ፀጥታውን ለማስከበር እየሰራ ቢሆንም በወንጀሉ ላይ የተሰማሩት ቡድኖች በአካባቢው ማህበረሰብ ውስጥ ሰርገው በመግባታቸው ሂደቱን አስቸጋሪ እንዳደረገው ክልሉ ገልጿል፡፡ጉዳዩ በክልሉ  መንግስት ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ የአካባቢው ማህበረሰብ ወንጀለኞችን በማጋለጥና የእስር ማዘዣ የወጣባቸውን በመጠቆም አካባቢውን ወደ ቀደመ ሰላም ለመመለስ ጥረት መደረግ አለበትም ተብሏል፡፡

የአማራ ክልል በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር የተፈጠረውን ግጭት ለመቆጣጠር የፌደራል መንግስት መከላከያን ጨምሮ ትብብር እንዲያደርግም ጠይቋል፡፡ይህ ካልሆነ ግን ችግሩ እየሰፋ በአካባቢው የሚደርሰውን ውድመትና ጥፋት ክፉኛ እንደሚያባብሰው የክልሉ መንግስት ኮሙኑኬሽን አቶ አሰማኻኝ አስረስ ተናግረዋል፡፡

ግጭቱ በአማራና በቅማንት ህዝቦች መሃል ሳይሆን በሶስተኛ ወገን ተልዕኮ የተሰጣቸው ቡድኖች እየፈጠሩት ያለ ችግር መሆኑንም አቶ አሰመኻኝ ለኢቢሲ ገልፀዋል፡፡

በስመኘው ይርዳው