Back

በስልጤ ዞን ወራቤና በትግራይ አቢ አዲ ከተሞች በ10ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የዓይን ህክምና ሊሰጥ ነው

የካቲት 22፣2011

አልባሰር ኢንተርናሸናል ፋውንዴሽን በቀጣይ 15 ቀናት ውስጥ በስልጤ ዞን ወራቤና በትግራይ ክልል አቢ አዲ በ10ሺህዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን የአይን ህክምና ሊሰጥ ነው፡፡

የአልባሰር ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን የተባለዉ የበጎ አድራጎት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ሀጂ ያሲን ራጁ የህክምና ቡድኑ   የካቲት 26 እና 27 ወደ ደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ወራቤ አጠቀላይ ሆስፒታል ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ለአይነ ስውርነት ለተጋለጡ ሰዎች የዓይን ህክምና ይሰጣል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ቡድኑ ወደ ትግራይ ክልል ተምቤን አቢ አዲ በማቅናት መጋቢት 7 ተመሳሳይ አገልግሎት እንደሚሰጥም ተወካዩ ተናግረዋል፡፡

አገልግሎቱ በሚሰጥባቸው አካባቢዎች ካሉ አጎራባች ክልሎችና ዞኖች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችም ህክምናውን መጠቀም እንደሚችሉ ሀጂ ያሲን ለኢቢሲ ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ ከ5 ወር በፊትም በአዲስ አበባ አለርት ሆስፒታልና በአክሱም በተሰጠ የነፃ የህክምና አገልግሎት 1ሺህ 1መቶ የሚሆኑ ዜጎች የዓይን ብርሃነቸዉን እንዲያገኙ የሚያስችል አገልግሎት አብርክቷል፡፡

የአልባሰር ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ አገልግሎቱን መስጠት ከጀመረ ከ15 ዓመታት በላይ 20ሺ ለሚሆኑ ሰዎች የዓይን ህክምና ሰጥቷል፡፡

በሙሐመድ ፊጣሞ