Back

በአገሪቱ ካሉ 11 ከተሞች ከ440ሺህ በላይ ሰዎች በከተሞች የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር ታቅፈዋል

የካቲት 13፣2011

በከተሞች የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር ከ440ሺህ በላይ ታቅፈው ተጠቃሚ መሆናቸውን በፌደራል የስራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ በተቀረጸው የከተሞች የምግብ ዋስትና መርሃግብር እስካሁን በ11 ከተሞች በመተግበር ላይ መሆኑን ኤጀንሲው አመልክቷል፡፡

በኤጀንሲው የምግብ ዋስትና ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰለሞን አሰፋ በተለይ ለኢቢሲ እንደተናገሩት ፕጀክቱ መተግበር ከጀመረበት ከ2009 ጀምሮ 440 ሺህ 885 ሰዎችን ተጠቃሚ ማድርግ ተችሏል ::

ለ 5 አመት በሚቆው የመጀመሪያው ዙር ፕሮጀክት መርሃ ግብር ከተያዘው እቅድ አንፃር 72 በመቶው ወደ ትግበራ ተገብቷል ያሉት ምክትል ኃላፊው ፣በቅርቡ ቀሪ 141 ሺህ ሰዎች ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተመልክቷል ፡፡

በመርሃግብሩ አቅመ ደካሞችንና መስራት የማይችሉ አካል ጉዳተኞችን በቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን የመስራት አቅም ያላቸውን ደግሞ በአካባቢ ልማት እንዲሰማሩ በማድረግ ነው መርሃ ግብሩ እየተተገበረ ያለው ፡፡

እስከ ባለፈው አመት በአካባቢ ልማት ላይ ለተሰማሩት በቀን ይከፈል የነበረው 60 ብር ወደ 75 ብር ሲሻሻል ፣ ለአንደ ሰው 170 ብር የነበረው የቀጥታ ተጠቃሚዎች ወደ 215 ብር እንዲሻሻል ተደርጓል ተብሏል፡፡

አልምቶ ተጠቃሚዎች እንደ ከተሞቹ ሁኔታ በጽዳት ፣በአረንጓዴ ልማት፣በተቀናጀ ተፋሰስ ፣የከተማ ግብርና ቦታዎችን ምቹ በማድረግ እና በመሰረተ ልማት ስራዎች መሰማራታቸውን ኤጀንሲው አመልክቷል ፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ደስታ ካሳ በአልምቶ ተጠቃሚ ፕሮግራም በአካባቢ ጽዳት ተሰማርተው በሚያገኙት ገንዘብ ኑሮሯቸውን መደጎም እንዳስቻላቸው ለኢቢሲ ገልጸዋል፡፡

በን/ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 በአረጋውያን የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ መሆን የጀመሩት የ70 ዓመት አዛውንቱ አቶ አለሙ ታምራት በበኩላቸው የሚያኙት የገንዘብ ድጋፍ ጾም ከማደር እንዳዳናቸው ተናግረዋል፡፡

በሶስት ዙር በሚከናወነው ፕሮግራም በአካባቢ ልማት ላይ የተሰማሩ ተጠቃሚዎች ለሶስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን ከዚያም ወደ ዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ መርሃ ግብር እንደሚሸጋገሩም የከተሞች የምግብ ዋስትና መርሃግብር ምክትል ኃላፊ አቶ ሰለሞን አሰፋ ገልፀዋል፡፡

በዚህም የህይወት ክህሎት ፣ የፋይናንስ አጠቃቀም ስልጠና አጠቃላይ የራሳቸውን ኑሮ በራሳቸው እንዲያሸንፉ መሰረታዊ እውቀት እንዲይዙ ይደረጋልም ተብሏል፡፡
ከሚቀጥለው አመት ጀምሮ መርሃ ግብሩ ወደ ሌሎች ከተሞች እየሰፋ የሚሄድ በመሆኑ ህብረተሰቡ እገዛ ሊያደርግና ያሉትንም ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ለኤጀንሲው እንደያመላክት ምክትል ኃላፊው ጠይቀዋል፡፡

የከተሞች የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር ከአለም ባንክ በተገኘና ከኢትዮጵያ መንግስት በተመደበ 450 ሚሊዮን ዶላር በጀት በ2009 ጀምሮ በተመረጡ 11 ከተሞች ወደ ስራ ገብቷል፡፡

በማስተዋል መታፈሪያ