Back

በ2011 በጀት ዓመት የሕግ ጉዳዮችን ጨምሮ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል - የተወካዮች ምክር ቤት

ሐምሌ 4 ቀን 2011 ዓ.ም

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2011 በጀት ዓመት ሕግ ማውጣትን ጨምሮ በርካታ ሥራዎች ማከናወኑን በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

በሕግ ማውጣት በኩል 67 ረቂቅ አዋጆች ለቋሚ ኮሚቴዎች ሲመሩ፣ 62 የሚሆኑት ደግሞ መፅደቃቸው ነው የተገለጸው፡፡

32 የሚሆኑ አዋጆች በምክር ቤቱ የውሳኔ ሃሳብ እንደተሰጠባቸውና 2 የሚሆኑት ደግሞ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር በጋራ ውሳኔ እንደተሰጠባቸው ተገልጿል፡፡

ምክር ቤቱ 25 የሚኒስትር መስሪያ ቤቶች እና ፈፃሚ አካላትን መገምገሙንና የውሳኔ ሃሳብ ማቅረቡን ገልጿል፡፡

በተለይም ክፍተት አለባቸው የሚባሉ የትምህር ተቋማትን እና መከላከያ ሚኒስቴርን በመከታተል የወጪ ቅነሳ ብሎም የእቃ ግዢ ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ መሰራቱ ተገልጿል፡፡

ምክር ቤቱ በጤና፣ በትምህርት እና በመሰረተ ልማት ዘርፎች የመስክ ምልከታ ማድረጉም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

መራጭ ህዝብ እና ተመራጭ አባላት በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተገናኝተው ችግሮችን እንዲፈቱ ከማመቻቸት በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ስራዎች መሰራታቸው ተገልጿል፡፡

በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ሪፎርም በተመለከተም በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ነው የተገለጸው፡፡

በቀጣይም እስካሁን በወጡ ሕጎች ላይ ማሻሻያ የማድረግ ሥራ እንደሚከናወን ተጠቅሷል፡፡

ለረፍት ወደየአካባቢያቸው የሚያቀኑት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በክረምቱ ወቅት ከየመረጣቸው ማኅበረሰብ ጋር በመገናኘት ውይይት እንደሚያደርጉም ተገልጿል፡፡

ሪፖርተር፡- ተመስገን ሽፈራው