Back

በወባ በሽታ ይከሰት የነበረው የሞት ምጣኔ በ80 በመቶ መቀነሱን የጤና ሚንስቴር አስተወቀ

ሚያዚያ 16፣ 2011

በወባ በሽታ ይከሰት የነበረው የሞት ምጣኔ በ80 በመቶ መቀነሱን የጤና ሚንስቴር አስተወቀ፡፡


መከላከልን መሰረት ባደረገው የጤና ፖሊሲ መሰረት የወባ በሽታን ለመከላከል የተደረገው ጥረት ውጤት እያሳየ መሆኑን ሚኒስቴሩ አመልክቷል፡፡

በሚንስቴሩ የወባ መቆጣጠርና ማጥፋት ቡድን አስተባባሪ አቶ መብራህቶም ኃይለ ለኢቲቪ እንዳሉት በወባ በሽታ ይከሰት የነበረው አገራዊ የሞት መጠን በ80 በመቶና የህሙማን ቁጥር ደግሞ በ50 በመቶ መቀነስ መቻሉን በጥናት ተለይቷል፡፡

አጎበሮችን በማሰራጨት፣ ቤቶችን ኬሚካል በመርጨት፣ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግና የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎችን በማጠናከር 11 ሚሊዮን ህዝብን ከወባ በሽታ ተጋላጭነት መከላከል ተችሏልም ብለዋል፡፡

የወባ በሽታን ጨርሶ ለማጥፋት የወባ ማስወገድ ትግበራ የሚደረግባቸው 239 ወረዳዎችን በመምረጥ ወደ ተግባር መገባቱን በሚንስቴሩ የወባ መቆጣጠርና ማጥፋት ቡድን አስተባባሪ አቶ መብራህቶም ኃይለ ገልፀዋል ፡፡

የወባ ማስወገድ ኘሮግራምን ለማሳካትና የበሽታውን ስርጭት ለመግታት በህክምናው ረገድ የመድሃኒት አቅርቦት በሁሉም የጤና ተቋማት እየተሰጠ ይገኛልም ብለዋል፡፡

በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል አዲስ ወባ አስተላለፊ ትንኝ ተገኝቷል መባሉን ተከትሎ ትንኙ ለህብረተሰቡ ጤና ችግር መንስኤ መሆኑ አለመሆኑን በጥናት ለማረጋገጥ አየተሰራ መሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል ፡፡

የወባ ብሽታን ለመከላከል በሚል በየዓመቱ የሚከበረው የአለም የወባ ቀን ዘንድሮም ሚያዚያ 17፣2011 በድሬድዋ ከተማ ″ወባን ማጥፋት ከእኔ ይጀምራል″ በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡

በበዓሉም እያንዳንዱ ዜጋ ወባን በማስወገድ ሂደት ድርሻ እንዳለው ለማስገንዘብ፣ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግና አጋርነትን ለማጠናከር ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ሚኒስቴሩ አመልክቷል፡፡

በአበበ ሞላ