Back

በኮሌራ የተያዙ ዜጎች ቁጥር 871 ደረሰ፡- የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

ሰኔ 25፡ 2011 ዓ.ም

በሀገሪቱ 5 ክልሎች፣ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች 871 ሰዎች በኮሌራ በሽታ መያዛቸውን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

 

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ የበሽታውን ስርጭት አስመልክተው በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

 

ዶክተር ጌታቸው በመግለጫቸው የኮሌራ ወረርሽኝ በሽታ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በሶማሌና አፋር  ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳድሮች መከሰቱን ተናግረዋል።

 

በአሁኑ ወቅትም በአጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በኮሌራ ወረርሽኝ በሽታ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 871 ደርሷል ነው ያሉት ።

 

በዚህ መሰረትም በኦሮሚያ ክልል 360፣ በአማራ ክልል 202፣ በትግራይ ክልል 19፣ በአፋር ክልል 131፣ በሶማሌ ክልል 33፣ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ተናግረዋል።

 

እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ 125 ሰዎችና እና በድሬ ዳዋ ከተማ ደግሞ አንድ ሰው በበሽታው መያዛቸውን ገልፀዋል።

 

እስካሁንም በሀገር አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ በሽታ የ17 ሰዎች ህይወት ማለፉን ዶክተር ጌታቸው ተናግረዋል።

 

ከእነዚህ ውስጥም 14ቱ በአማራ ክልል፣ሁለቱ በኦሮሚያ ክልል እንዲሁም አንድ ሰው በአፋር ክልል መሆኑን አንስተዋል ። 

 

በሽታውን ለመቆጣጠርም ናሙናዎችን በጥናት በመለየትና በላቦራቶሪ በማረጋገጥ ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የመድሃኒትና የህክምና ግብዓት አቅርቦትእየተሰራጨ መሆኑ ተገልጿል።

 

ከዚህ ባለፈም በሀገርአቀፍ ደረጃ በሽታውን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ 26 የለይቶ ማከሚያ ማዕከላት መቋቋማቸው ነው የተገለፀው።

 

ባሳለፍነው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ዞን በሽታው በተከሰተባቸው ወረዳዎች 291 ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች የከሌራ በሽታ ክትባት መሰጠቱንም አንስተዋል።

 

 የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት