Back

150 በላይ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የህጻናት ማቆያ ማዕከላትን አቋቁመው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል

የካቲት 27፣2011

150 የፌዴራል እና ክልል መስሪያቤቶች የህጻናት ማቆያ መዕከላት አቋቁመው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የሴቶችና ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በመንግስት መስሪያቤቶች የህጻናት ማቆያ ማዕከላት እንዲቋቋሙ መመሪያው ከጸደቀበት ከነሀሴ 2010 ጀምሮ ቀድመው ወደ ስራ የገቡ መስሪያ ቤቶች ናቸው ማዕከሉን ያቋቋሙት፡፡

በሴቶች ፣ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች ተጠቃሚነትና ማካተት ዳይሬክተር ወ/ሮ ፈትያ ድልገባ  እንደገለጹት ማዕከሉን ያላቋቋሙ መስሪያቤቶች የቦታ እና የበጀት ችግር የገጠማቸው ናቸው ፡፡በተለይ አብዛኞቹ የፌዴራል መስሪያቤቶች በኪራይ የሚሰሩ በመሆናቸው የቦታ ጥበትና ምቹ ያለመሆን ችግር ጎልቶ ይስተዋላልም ብለዋል፡፡

የህጻናት ማቆያ መዕከላት እንዲቋቋሙ የተወሰነው ህጻናት የእናት ጡት ወተትን ቢያንስ ለስድስት ወር እንዲያገኙ እና ሴቶች በስራ ገበታቸው ተረጋግተው እንዲሰሩ እንዲሁም እንዳይቀሩ ለማስቻል አላማ በማድረግ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በጀት እንዲያዝ መመሪያ ወጥቶ ለማጸደቅ  በሂደት ላይ መሆኑ የጠቆሙት ወ/ሮ ፈትያ፣ ክልሎች የራሳቸው አሰራር ያላቸው  ቢሆንም መነሻ እንዲሆናቸውም ጭምር የበጀት ስራው በአጭር ጊዜ ተጠናቆ እንደሚጸድቅም ተናግረዋል፡፡

የበጀት እጥረት ባለባቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች በመመሪያው ላይ የቀረበውን መስፈርት ካሟሉ በሚጸድቀው በጀት ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል፡፡

መስሪያቤቶቹ የተቀመጠውን መስፈርት አሟልተው ወደስራ እንዲገቡ በመጀመሪያ የድጋፍና ክትትል ስራዎች ከተሰሩና የበጀት ድጋፍ ከተደረገ በኃላ ወደ አስገዳጅ ሁኔታ ይሸጋገራል ብለዋል ዳይሬክተሯ ፡፡

ችግሩን ለጊዜው ለማቃለል በፌዴራልም በክልልም ደረጃ ባላቸው ግብዓት ወደስራ እንዲገቡ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን በቀጣይ የማዋያ ማዕከላቱ ለህጻናቱ ጤንነት ምቹ ከማድረግ ጋር በተያያዘ ሁሉም በሚፈለገው ደረጃ እንዲሰሩ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ከትራንስፖርት ጋር በተያያዘ አሁን ላይ እናቶች በፐብሊክ ሰርቪስ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ  ከልጆቻቸው ጋር እንዲጓጓዙ ቢፈቀድም ከአዋቂዎች ጋር በተጨናነቀ መልኩ መጓዛቸው ለህጻናቱ ጤንትነት አስጊ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴርም ይህንን በመረዳት  በአንድ የጉዞ መስመር አንድ ባስ እንዲመደብ ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑም አመልክቷል፡፡

ፐብሊክ ሰርቪስ በየመስመሩ ምንያህል እናቶች እንዳሉ እያጠና ሲሆን ያንን ማድረግ የማይቻል ከሆነ የህጻናት ቦታ ተከልሎ የሚጓጓዙበት ሁኔታ እንደ አማራጭ ተቀምጧልም ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ  ኮርፖሬሽን ፣የዕንባ ጠባቂ ተቋም ፣የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና ሌሎችም የህጻናት ማቆያ ማዕከል አቋቁመው  ሙሉ በሙሉ ወደስራ ከገቡ መስሪያ ቤቶች ይገኙበታል፡፡ የቁሳቁስ ግዢ አጠናቀው በጀት ያስፈቀዱም በሂደት ላይ ያሉ መስሪያ ቤቶች መኖሪያቸውም ተመልክቷል፡፡

ሪፖርተር፡-ማስታዋል መታፈሪያ