Back

17 ሺህ የሚሆኑ የጎዳና ላይ ነጋዴዎችን ህጋዊ ሆነው እንዲሰሩ ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገለፀ

የካቲት 26፣2011

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቋሚ መነገጃ የሌላቸው ወገኖችን ጉዳይ መፍትሄ ለመስጠት እቅድ አውጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በከተማ አስተዳድሩ የንግድና ኢንዱስትሪ መደበኛ ያልሆነ ንግድ ሥርዓት ማስያዝ ዳይሬክተር አቶ ዳኛቸው ሉሌ እንደገለፁት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች የሚካሄድ የጎዳና ላይ ንግድ ስርዓት እንዲይዝ እየተሰራ ነው፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት በሮው 58 ሺህ የሚሆኑ የመደበኛ መነገጃ ቦታ የሌላቸው  ዜጎች መመዝገቡንና 32ሺህ ያህሉ በደንብና በመመሪያ ታቅፈው መታወቂያና የስራ አጥ መታወቂያ መውሰዳቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

መታወቂያና የስራ አጥነት ካርድ ካገኙ ወገኖች መካከል 17 ሺህ የሚሆኑት ወደ ስራ መግባታቸውን ነው አቶ ዳኛቸው ያስረዱት፡፡

ግለሰቦቹ ከገቢዎች የንግድ ምዝገባ መለያ ቁጥር (tin no.) እያወጡ በመምጣት ባጅ እየተሰጣቸው ወደ ስራ እየተሰማሩ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ቀሪዎቹን መታወቂያ ይዘው የሚጠባበቁ ወገኖች በተያዘው የመካከለኛ ጊዜ እቅድ ወደ ስራ የማስገባት ሂደቱ እንደሚቀጥልም ተመልክቷል ፡፡

በቀጣይም፣ መታወቂያ የሌላቸውን ወገኖች በተመለከተ ከከተማ አስተዳደሩ አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ከአዲስ አበባ ንግድን ኢንዱስትሪ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

በዮሴፍ ለገሰ