በሁሉም የቱሪስት መዳረሻዎች አስተማማኝ ሰላም አለ:- የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር

በርካታ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻዎች ያሏት ኢትዮጵያ በሁሉም የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላም መኖሩን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር  መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን የሚጎበኙ ቱሪስቶችን ደህንነት በአስተማማኝ መልኩ ለመጠበቅ እና ሰላማዊ የጉብኝት ሂደትን ለማስፈንም የቱሪዝም ዘርፍ ንዑስ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞም እየተሰራ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያነሳቸውን ትክክለኛና ህጋዊ ጥያቄዎች  በውጭ አገራት በሚኖሩ ፅንፈኛ ቡድኖች ወደ ብጥብጥና ግርግር ለመለወጥ ቢሞከርም በአገር ወዳድ ህዝብና በመንግስት ከፍተኛ ጥረት ሊረጋጋ ችሏል፡፡

የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ለቱሪስቶች ሙሉ ጥበቃ እንደሚያደርግና በአገሪቱ ውስጥ እስካሁን በቱሪስቶች ላይ አንዳችም ጉዳት እንዳልደረሰ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ሁሉም የቱሪስት መዳረሻዎች አስተማማኝ ሰላም መኖሩንም ተመልክቷል።

የቱሪስቶችን ደህንነት በአስተማማኝ መልኩ ለመጠበቅ የተቋቋመው የቱሪዝም ዘርፍ ንዑስ ኮማንድ ፖስትም የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ነው፡፡

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2017 መጎብኘት ካለባቸው አስር ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን በቱሪዝም ላይ ትኩረት ያደረገው ሎንሊፕላኔት ድረ ገጽ በቅርቡ ይፋ አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያ ባላት ዘመን አቆጣጠር፣ የራሷ ጽሁፍ፣ ቋንቋዎች፣ ምግብ፣ ቤተ እምነቶችና ቡና ተመራጭ ሆናለች ብሏል ድረ ገጹ፡፡

በሰሜን ተራሮች ላይ የሚገኙ ብርቅዬ እንስሳት፣ በትግራይ ክልል ያለው የደብረ ዳሞ ገዳምና በጣና ሃይቅ ላይ ከሚደረግ የጀልባ ጉዞ በኋላ የሚገኙት ጥንታዊ ገዳማት የጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ ረገድ ትልቅ ቦታ አላቸው ተብሏል፡፡

ሳቢ የመልክዓምድራዊ አቀማጥ ያላት ኢትዮጵያ ወደ ቱሪስት መዳረሻዎች የሚያደርሱ አዳዲስ የአውሮፕላን መስመሮች በመዘርጋት ለቱሪስቶች አማራጭ መፍጠሯም ተገልጿል፡፡

ቱሪስቶች ኢትዮጵያን እ.አ.አ በ2017 ቀዳሚ ምርጫቸው እንዲያደርጉ ድረ ገጹ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

ከ900 ሺህ በላይ የሚሆኑ ቱሪስቶች ባለፈው አመት ብቻ ኢትዮጵያን የጎበኙ ሲሆን የአስጎብኝ ድርጅቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱና ወደ ቱሪዝም መዳረሻዎቹ አስተማማኝ ትራንስፖርት አማራጮች መኖራቸው የቱሪስት ፍሰቱ እንዲያድግ አድርጎታል፡፡

በናትናኤል ፀጋዬ