የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን

የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን   

ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም የፀደቀው የፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ ሕገመንግስት መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ከዳር እስከዳር በማሳተፍ በየአመቱ ይከበራል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከመራር ትግል በኋላ የመሠረቱት የፌዴራል ስርዓት በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተና ህብረ ብሔራዊ አንድነት የፈጠረ ፤ እንዲሁም የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች  በአል መከበር በህገ መንግስቱ የተቀመጠው አንድ የጋራ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ራእይን እውን ያደረገ እንደሆነም ይታመናል፡፡

የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት የጸደቀበት ህዳር 29 የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ተብሎ በአገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት እንዲከበር የተወሰነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሚያዚያ 21 ቀን 1998 ዓ.ም ባካሄደው ሶስተኛው የፓርላማ ዘመን አንደኛ አመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ነበር።

በአገራችን የመጀመሪያው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በ1999 ዓ.ም በአዲስ አበባ ነበር የተከበረው፡፡

በአሉ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አዘጋጅነት በመዲናይቱ ሲከበር መሪ ቃሉ "ሕገ-መንግስታዊ ቃል ኪዳን የአብሮነታችን መገለጫ ነው" የሚል ነበር።

2ኛው በዓል ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ማእከል በሆነችው ሀዋሳ ላይ በድምቀት ሲከበር መሪ ቃሉም "ልዩነታችን ውበታችን ውበታችን አንድነታችንና ጥንካሬያችን ነው" የሚል ነበር።

3ኛው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በ2001 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አዘጋጅነት በአዲስ አበባ "ዴሞክራሲያዊ አንድነታችን በማጠናከር ልማታችንን እናፋጥናለን" በሚል መሪ ቃል ተከበረ።

4ኛው በዓል በድሬዳዋ አስተዳደርና አጎራባች ክልሎች ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ኢትዮጵያ ሶማሌ፣ እና ሀረሪና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በአንድነት በድሬዳዋ በ2002 ዓ.ም የተከበረ ሲሆን መሪ ቃሉ "መቻቻል ለዴሞክራሲያዊ አንድነትና ልማት" የሚል ነበር፡፡

5ኛው ከአለምአቀፍ የፌዴራል ቀን ጋር በማያያዝ በ2003 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተከበረ ሲሆን መሪ ቃሉም "የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እጅ ለጅ ተያይዘን የአገራችንን ህዳሴ ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ እናደርሳለን" የሚል ነበር፡፡

6ኛው በትግራይ ክልላዊ መንግስት አዘጋጅነት በመቀሌ በ2004 ዓ.ም ሲከበር መሪ ቃሉ "ሕገ መንግስታችን ለብዝሀነታችን ለአንድነታችንና ለሕዳሴችን" የሚል ነበር፡፡

7ኛው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ደግሞ በአማራ ክልላዊ መንግስት አዘጋጅነት በባህር ዳር በ2005ዓ.ም የተከበረ ሲሆን መሪ ቃሉም "ብዙም አንድም ሆነን በመለስ ራዕይ በሕገ-መንግስታችን ለሕዳሴያችን" የሚል ነበር፡፡

8ኛው ዙር ደግሞ በሶማሌ ክልላዊ መንግስት አዘጋጅነት በጅግጅጋ የ2006 ዓ.ም የተከበረ ሲሆን መሪ ቃሉም "ሕገ-መንግስታችን ለህዳሴያችን" የሚል ነበር፡፡

9ኛው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በቤንሻንል ጉምዝ ክልላዊ መንግስት አዘጋጅነት በአሶሳ ከተማ "በህገ-መንግስታችን የደመቀው ኢትዮጵያዊነታችን ለህዳሴያችን" በሚል መሪ ቃል ነበር የተከበረው።

10ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን "የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተሳትፎ ለላቀ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን" በሚል መሪ ቃል በጋምቤላ ከተማ ነበር የተከበረው፡፡

"ሕገመንግስታችን ለዲሞክራሲያዊ አንድነታችንና ህዳሴያችን" በሚል መሪ ቃል ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በጥንታዊቷ የሐረር ከተማ ይከበራል፡፡   

የ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል "ህገ መንግስታዊ ስርአታችን ለዘላቂ ልማታችን መሰረተ ነው"፣ "በመከባበርና በመቻቻል ላይ የተመሰረተ አንድነታችን ህዳሴያችን እውን ይሆናል" የሚሉና ሌሎችም መልእክቶች የሚተላለፉበት መድረክ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

11ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ስኬታማ በሆነ መንገድ ለማክበር አዘጋጁ የሐረሪ ክልል ህዝብና መንግስት ዝግጅቶቻቸውን አጠናቀዋል፡፡

ብሔሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች የፌዴራል ስርዓቱ ያስገኛቸውን ጥቅሞች ሊያስጠብቁና የሀገሪቱ ብሔሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች የፌዴራል ስርዓቱ ያስገኛቸውን ጥቅሞች ዘላቂነትና በአስተማማኝነት ሊያስጠብቁ እንደሚገባም መንግስት በተለያዩ ጊዜያት በሚከበሩ በአላት ላይ አስገንዝቧል፡፡

የዜጐችን የማንነት፣ የባህል፣ የታሪክና የሃማኖት ብዝሃነትን በህገመንግስታዊ አግባብ ማስተናገድ የቻለና የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚደክሙላት የጋራ ሀገር እንዲኖራቸውም ያደረገ ነው፡፡

የፌዴራል ስርዓቱ የኢትዮጵያ ህዝቦች የተነፈጉትን የታሪክ የቋንቋ፣ የባህልና ሌሎች የማንነት መገለጫዎች ለማስከበርና ለማበልፀግ የሚያስችል ነው፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሀዝቦች የማንነታቸው መገለጫ የሆነ ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውንና ሃይማኖታቸውን መጠበቅና ማበልፀግ ችለዋል ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋዎቻቸው ማስተማርም ችለዋል፡፡

ባለሁለት አሃዝና ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት አስተማማኝ ሰላምና ተስፋ ሰጪ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስመዝገብ የቻለና የሀገሪቱ ፌዴራል ስርዓት ባለፉት 25 አመታት በሁሉም ዘርፍ በማሽቆልቆል ጉዞ ላይ የነበረችውን ሀገር ታሪክ የቀየረ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ህዝቦች የጀመሩትና እያጣጣሙ የሚገኙት ይህ ለውጥ የፌዴራል ስርዓቱ ያስገኘው ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ውጤት ነው፡፡

በናትናኤል ፀጋዬ