የውቧ ሐረር መገለጫዎች!

የሀረሪ ህዝብ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖሩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ውስጥ አንዱ ሲሆን የራሱ የሆነ ባህል፣ ቋንቋ፣ ስነ ልቦናዊ ዘይቤ እና መልክዓ ምድራዊ አሰፋፈር ያለው ህዝብ ነው፡፡

የሀረሪ ህዝብ ታሪክ ፣ ባህል እና ማንነት ከሐረር ከተማ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡

ሀረር ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀሱ እንዲሁም የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ በርካታ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ቅርሶች ባለቤት የሆነች ከተማ ናት፡፡ ከእነዚህ ቅርሶች መካከልም የከተማው ልዩ መለያ ምልክት ከመሆንም አልፎ እ.ኤ.አ በ2006 በዩኒስኮ በአለም ቅርስነት የተመዘገበው የጀጎል ግንብ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡

የጀጎል ግንብ  በወቅቱ የከተማዋ ገዢ በነበሩት በአሚር ኑር አማካይነት የጠላት ወረራን ለመከላከል በሚል  እ.ኤ.አ በ1551 እንደተገነባም ይነገራል፡፡ በግንብ ውስጥ ከ82 በላይ መስኪዶች እና በርከት ያሉ የሀረሪ ባህላዊ ቤቶች ይገኛሉ፡፡

የሐረር ጁጎል ግንብ ኢትዮጵያ በዩኒስኮ በአለም ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው አሥር ቅርሶች መካከል አንዱ ነው፡፡ የጀጎል ግንብ የሀረሪ ህዝብ የኪነ ህንፃ ችሎታውን የሚያስመሰክር የታሪክ እና የጥበብ መዘክር ነው፡፡

ግንቡ አምስት በሮች ሲኖሩት 24 የጥበቃ ማማዎችም አሉት፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን ከሁለቱ ማማዎች በስተቀር ሌሎቹ ፈርሰዋል፡፡ በእያንዳንዱ በሮች አቅራቢያም ወንዝና ምንጮች ይገኛሉ፡፡ የጀጎል ግንብ /ወራባ ኑዱል/ የጅብ መግቢያ ቀዳዳዎችም አሉት፡፡

አምስቱ በሮች በተለያዩ ቋንቋዎች ስያሜዎች ይጠራሉ፡፡ የበሮቹ መጠሪያ በሀረሪኛና በአማርኛ አስመእዲን በሪ /ሸዋ በር/፣ በድሪ በሪ /ቡዳ በር/፣ ሱግጣጥ በሪ /ሠንጋ በር/፣ አርጎባ በሪ /ኤረር በር/  እና  አሱሚይ በሪ /ፈላና በር/ ይባላሉ፡፡

ሐረር ከቅርስነት ባሻገር እ.ኤ.አ በ2003/4 በሰላም፣ በመቻቻል እና በመፈቃቀር ከተማነት አለም አቀፍ ሽልማት እና እውቅናን አግኝታለች፡፡ ይህም የተለያዩ  እምነት፣ ባህል እና ቋንቋ ያላቸው ህዝቦች ለዘመናት በሰላም እና በፍቅር የኖሩባት እና ዛሬም የሚኖሩባት ከተማ በመሆኗ የተቀዳጀችው ክብር እና እውቅና ነው፡፡

ሐረር ሌሎችም ሊጎበኙ የሚገቡ የቱሪስት መስህቦች ያሏት ከተማ ነች፡-የሐረሪ የባህል ሙዚየም፣ የባለቅኔው ራምቦ ማዕከል፣ አስደናቂው የጅብ ትርዒት እና ሌሎችም… ፡፡

ዘንድሮ የ2009 ዓ.ም 11ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በውቧ ሀረሪ ክልል "ሕገመንግስታችን ለዲሞክራሲያዊ አንድነታችንና ለህዳሴያችን"፣ በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡

በሰላም ፣ በመቻቻል እና በመፈቃቀር እውቅናን ያገኘችው ሐረርም በተለመደው የእንግዳ ተቀባይነት ልምዷ እንግዶቿን ተቀብላ ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃለች፡፡  

ቀጣዩን ሊንክ በመጫን በሐረር ከተማ የቱሪስት መስህብ ቦታዎች እና ባህላዊ ቅርሶች ላይ የተሰራውን ቅኝት ይመልከቱ፡-

 

ምንጭ፡-የሐረር ከተማ ታሪክ

 

በሐና ግርማ