የሀይል ሚዛን ለውጥ ውልደት የሆነው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ

በአብዱልአዚዝ ዮሱፍ

መጋቢት 13፣ 2009

ኢትዮጵያ ከክርስቶስ ልደት በኃላ 2ሺኛ ዓመቷን ስትቀበል ዘመኑን የኢትዮጵያ ሚሊኒዮም ብላ ሰይማው ነበር፡፡ አገሪቱ 20 ክፍለ ዘመናትን ማንነቷን አስጠብቃ የአፍሪካዊያን ተምሳሌት እስከመሆን የደረሰች በመሆኗ የአዲሱ ዘመኗን ብሩህ ተስፋ ሰንቃ ስትቀበለው ያለምክንያት አልነበረም፡፡

የኢትዮጵያ ሚሊኒዬም እንደገባ ለአገሪቱ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ጭምር የሰነቀው የመጀመሪያው የእድገትና ትራስፎርሜሽን ዕቅድ ከሚሊኒዬሙ መባቻ በፊት ለነበሩ ጅምር ዕምርታዊ ለውጦችን  አዲስ ምዕራፍ ከፋች ነበር፡፡

በተለይም አገሪቱን  በመንገድ፣ በባቡር፣ በኃይል ማመንጫ፣ በኢንዱስትሪና በሌሎችም ዘርፎች የተወጠኑ ከፍተኛ የበጀት የሚጠይቁ በመሆናቸው ለብዙ አፍሪካዊያንም ማነቃቂያ ደወል እስከመሆን ደርሷል፡፡

የናይጄሪያው ፕሮሼር ድረ ገጽ "Nigeria and Lessons of Ethiopia's Development Model" በሚል ርዕስ ያወጣው ጽሁፍ፤ ለረጅም ጊዜ ታቅዶ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች የአፈጻጸም ስኬትን ናይጄሪያ ከኢትዮጵያ ልትማራቸው ከሚገቡ ልምዶች መካከል አንዱ መሆኑን በመጥቀስ መስከረም 2009 ዓ.ም አስነብቦ ነበር፡፡

እኤአ በ2015 የግሎባል ቼንጅ ፎር አፍሪካ "Global Change for Africa Awards" ተሸላሚ የሆነው ይኸው ድረ ገጽ፤ ኢትዮጵያ በ2025 መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ለመሆን የተለመቻቸው ዕቅዶችን ለአብነት ይጠቅሳል፡፡

ኢትዮጵያ በረጅም ጊዜ አቅዳ ከምታከናውናቸው በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል በሚሊኒዮሙ ማግስት በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ጎልቶ የሚታየው የቀድሞው የሚሊኒዬም ግድብ የአሁኑ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በዋናነት ተጠቃሽ እንደሆነ ድረ ገፁ በአብነት ይጠቅሳል፡፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያዉያን የአገራዊ መግባባትና የኩራት ምንጭ በመሆን ካለው ፋይዳ አንስቶ ግድቡ በተፋሰሱ አገራት የወደ ፊት ዕጣ ፋንታ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽዕኖ ፕሮሸር ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡

የአካባቢያዊ ሀይል ሚዛን ለውጥ ውጤት

መቀመጫውን በሲውድን ስቶክሆልም ያደረገው የአለም አቀፉ ውኃ ተቋም እ.ኤ.አ በ2016 ያካሄደው ጥናት በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የአካባቢያዊ አገራት የኃይል ሚዛን ለውጥ ውጤት መሆኑን ያስረዳል፡፡

ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ያስመዘገበቻቸው ኢኮኖሚያዊና ዲኘሎማሲያዊ ድሎች የመደራደር አቅሟን ማሳደግ መቻላቸውን የተቋሙ ኘሮግራም ስራ አስኪያጅና የጥናቱ ቡድን መሪ ዶ/ር አና ክስካዎ ይገልፃሉ፡፡ በአባይ ተፋሰስ አካባቢ አገራት ዘንድ የኢትዮጵያ ተቀባይነት ማደግ ከዲሞክራቲክ ኮንጐ በስተቀር ሁሉም የታችኛዎቹ የተፋሰሱ አገራት የትብብር ማዕፍ Cooperative Framework Agreement (CFA) መፈረም ችለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ስምምነቱን ግንቦት 2002 ዓ.ም ቀድማ በመፈረም ለአገራቱ አርአያ መሆን መቻሏን የአለም አቀፉ ውሃ ተቋም ጥናት ያመለክታል፡፡

በሌላ በኩል የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሱዳን ያለውን ፋይዳ ከፍተኛ መሆን የሱዳን ሳይንቲስቶች በተደጋጋሚ መግለፃቸው፤ ሱዳን በግድቡ ያላት አቋም እየለዘበ እንዲሄድ ማድረጉና የኃላ ኃላ ድጋፏን እስከመስጠት ደርሳለች፡፡ በመሆኑም በዋናነት በግብፅ ብቻ የቀጠለው ተቃውሞ የላይኛዎቹን ተፋሰስ አገራት ተፅዕኖ በከፍተኛ ደረጃ እንደቀነሰው በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸው ኢኮኖሚያዊና ዲኘሎማሲያዊ ድሎች ምክንያት የአካባቢውን የኃይል ሚዛን መለወጥ መቻሏ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውልደት ምክንያት መሆኑን የአለም አቀፉ ውሃ ተቋም ጥናት ያመለክታል፡፡

የአባይ ተፋሰስ አገራትን የትብብር አቅጣጫ መልክ ማስያዝ

የአፍሪካ ቢዝነስ መጽሔት "ኢትዮጵያ ካታሊስት ኦፍ ዘ ሆርን ኦፍ አፍሪካ ሀምሌ 2008 ዓ.ም "Ethiopia Catalyst of the Horn of Africa" በሚል ርዕስ ኢትዮጵያን ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በተነተነበት ፅሁፉ፣ "ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ሌሎችን የምትፈልግ አገር ነበረች፤ ነገር ግን አሁን ሁኔታዎች ተቀይረው ኢትዮጵያ በሌሎች አገራት ተፈላጊ አገር ናት" ሲል ያትታል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአገሪቱን ኃይል ፍላጐት ከማሟላት በተጨማሪ አካባቢያዊ አገራት የተሳሰረ ኢኮኖሚ እንዲኖራቸው አንዲሁም የተረጋጋ ቀጠና እንዲፈጠር የራሱን ሚና እንደሚጫወት የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለ15 ዓመታት ሳይሳካ የዘለቀውን የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ (Nile basin initative) ግብ እውን ሊያደርግ ይችላል በማለት የአለም አቀፉ ውሃ ተቋም ግምቱን አስቀምጧል፡፡

ከዚህ ባሻገር በናይል ተፋሰስ አገራት ዘልቆ የቆየውን ውዝግብ መልክ እንዲይዝ በማድረግ የተፋሰሱ አገራት የጋራ ኘሮጀክት ቀርፀዉ በጋራ የሚያለሙበት እውነተኛ የተፋሰስ አገራቱ የትብብር ድርጅት ውልደት ምክንያት ይሆናል በማለት የአለም አቀፉ ውኃ ተቋም ኘሮግራም ማኔጀር ዶ/ር አና ክስካዎ የጥናት ውጤት ያመለክታል፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሳይጠናቀቅ ከወዲሁ የአካባቢው አገራት ከኢትዮጵያ ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ስምምነት እየፈፀሙ መሆናቸውን ጥናቱ በማሳያነት ያቀርባል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የኤሌክትሪክ ኃይልን ወደ ኬንያ፣ ሱዳንና ጁቡቲ ለመላክ በሂደት ላይ መሆኗ  (ለሱዳን 100 ለጅቡቲ 29 ሜጋ ዋት መላክ ጀምራለች) እንዲሁም የታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ግድቦች ሲጠናቀቁ ለተጨማሪ ሰባት አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት እንደሚደረግ የኢትዮጰያ ኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን ገልጿል፡፡

ከታዳሽ የኃይል ምንጮች 6ዐ ሺህ ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ዕምቅ አቅም ያላት ኢትዮጵያ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ታንዛኒያ፣ ቡሩንዲና ሩዋንዳ ለመላክ ከአገራቱ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርማለች፡፡ ደቡብ ሱዳን ኡጋንዳና የመን የኤሌክትሪክ ሀይልን ከኢትዮጵያ ለማስገባት ዕቅድ ያላቸው መሆኑን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፒተር ሙንጋይ፤ ከኢትዮጵያ በምናስገባው የኤሌክትሪክ ኃይል፤ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አሁን ያለውን 10 በመቶ የጠቅላላ ሀገራዊ ምርት ድርሻ፤ ወደ 15 በመቶ ለማሳደግ ያለመ መሆኑን መናገራቸው፤ የኢትዮጰያ ከጐረቤት አገራት ጋር ተሳስሮ አብሮ የማደግ ፖሊሲ እየሰመረ ለመምጣቱ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡

ግብጽ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን የተፈራረሙት የሶስትዮሽ ስምምነትም ግንኝነቱ እየተሻሻለ ለመምጣቱ ማሳያ ነው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  ግንባታ የአገራዊ መግባባትና የኩራት ምንጭ

እ.ኤ.አ በ1964 የተጠናቀቀው የግብፅ አስዋን ግድብ ለአሁኑ ግብፃዊያን ስነ-ልባናዊ ማንነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን በግብፅ መንግስታዊ ጋዜጣ አህራም ላይ የሰፈረው ጽሑፍ ያስረዳል፡፡ በወቅቱ የግብፅ ኘሬዝዳንት የነበሩት ጀማል አብዱልናስር ያደረጉት ንግግር የግብፅ አገራዊ አንድነት ለማምጣት ያለመ ነበር፡፡

ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው "የአስዋን ግድብ የግብፅ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ አገራዊ እንዲሁም ወታደራዊ ጉዳዮችን እንደ አንድ ጠንካራ የአለት ድንጋይ ያጠበቀ ግድብ ነው፤ የናይል ውኃ  የኩራታችን ምንጭ ወደ ሆነ የአማለችን ትልቅ ሀይቅ መቀየር ችለናል" ብለው ነበር፡፡

የግብጹ አስዋን ግድብ የፈጠረው አገራዊ አንድነትና ኩራት የግብጻዉያን የጋራ እሴት ምንጭ ሆኖ እስከ አሁን ድረስ ዘልቋል፡፡  

በተመሳሳይ ታላቁ የህዳሴ ግድብም ህብረ ብሔራዊነትን ለተላበሰችው ኢትዮጵያ አንድ የሆነ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ መገንባት የሚያስችል ኘሮጀከት መሆኑን በተደጋጋሚ ይገልፃል፡፡

ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያዊነትን በአባይ ወንዝ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔርብሔረሰቦችና ህዝቦች እንደ ገባር ወንዞች በመግለጽ ኢትዮጵያዊነት በህብረ ብሄራዊነት የተገነባ መሆኑን በሰጡት ትንታኔ  ሲያስቀምጡ ያለምክኒያት አልነበረም ፡፡ እንዲያውም አባይ  በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ካለው ቦታ በመነሳት ወደፊት ስለሚጫወተው ሚና ከግምት ውስጥ በማስገባት ነበር፡፡

መጋቢት 24፣2003 የግንባታው ጅማሮ በጠቅላይ ሚንስትር የተበሰረው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 6ኛ አመቱ ላይ ሲደርስ ኢትዮጵያዊያኑን በማስተበበር ከጫፍ እስከ ጫፍ እንዲነቃነቅና እንዲተባበር እያደረገ ያለ ታላቅ ህዝባዊ ፕሮጀክት በመሆኑ ነው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብሔራዊ የኩራት ምንጭም ነው፡፡ የህዳሴው ግድብ አባይ ወንዝን በመገደብ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ወራሪ ኃይልን በማንበርከክ የፃፉትን ታሪክ፤ ድህነትንም በማሸነፍ በኢኮኖሚው ዘርፍ ደግሞ ታላቅ ታሪክ የሚጽፉበት አጋጣሚ መሆኑን መንግስት በተደጋጋሚ ይገልጻል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ በጥቁር ህዝቦች ታሪክ ሁለት ታላቅ ታሪኮች መስራቷን ገልጸው፤ የመጀመሪያው ኢትዮጵያ የወራሪ ኃይልን አንበርክካ የመለሰችበት ታሪኳ ሲሆን፤ ሁለተኛው ማንም አይደፍረውም የተባለውን   አባይ ወንዝ የውጭ ዕርዳታ ሳትጠብቅ በህዝቦች ተሳትፎ እየገነባችው ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በቅርቡ የኤሌክትሪክ ሀይል ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቀውና 56 በመቶ ግንባታው ፍጻሜ ያገኘው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፤ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት 6ኛው ዓመቱ የፊታችን መጋቢት 24 ፣2009 በግንባታው ቦታ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ  ኢትዮጵያዊያን በተገኙበት ይከበራል፡፡ ፕሮጀክታቸው የደረሰበትን ሂደት በአካል ተገኝተው የሚታዘቡ ይሆናል፡፡

በእርግጥም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ 6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት በማመንጨት ለአገሪቱ የአሌክትሪክ ኃይል ከማቅረብ ባለፈ ኢትዮጵያ በራሷ የህዝብ ድጋፍና በጀት መስራቷ ገና ከወዲሁ ፕሮጀክቱ የጂኦ ፖሊቲካ ጥቅሞቿን ማስከበሪያ መሳሪያ እየሆነ መምጣቱን የሚገልፁም አልጠፉም፡፡

በተለይም አረንጓዴ የኃይል ልማትን መሰረት ያደረገው ይኸው የኢትዮጵያ ፕሮጀክት አህጉራዊ ውህደቱንና ትስስሩን በመምራት ረገድ አፍሪካዊያንም ሆኑ ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀር በጉጉት እንዲጠብቁት አድርጓቸዋል፡፡

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ  ፕሮጀክት ከአፍሪካ 1ኛ ፣ከአለም 6ኛ መባሉ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በታሪኳ ደፍራው በማታውቀው ወንዝ ላይ አሃዱ ያለችበትን ግዙፍ ፕሮጀክት መገንባት መጀመሯ ብዙዎች ከዚህ የበለጠ የኃይል ሚዛን ማስጠበቂያ መሳሪያ አለ ወይ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡