የአይዳ ሙሉነህ የፎቶግራፍ ስራዎች በፓሪስ ኤግዚቢሽን ሊቀርቡ ነው

መጋቢት 19፡2009

በትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አይዳ ሙሉነህ የተዘጋጁት የኢትዮጵያን ትናንት እና ነገን የሚያሳዩት አፍሪካዊ ስራዎች አፍሪከስ ካፒታልስ "Afriques Capitales," በሚል ርዕስ በፈረንሳይ ፓሪስ በተዘጋጀ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን ለእይታ ሊቀርቡ ነው፡፡

በአፍሪካ ስራዎች ላይ የሚያተኩሩ ፎቶግራፎች የሚቀርቡበት አውደ ርዕይ በፓሪስ አይረን ኤንድ ግላስ የባህል ማዕከል ከነገ ጀምሮ እስከ ግንቦት 20 ለእይታ ክፍት ይሆናል፡፡

በሴቶች፣ በአፍሪካዊ ማንነት፣ በባህልና በአገር ላይ የሚያተኩሩት የአይዳ ሙሉነህ የፎቶ ስራዎችም በፌስቲቫሉ ላይ ይቀርባሉ፡፡

አይዳ የኢትዮጵያን ባህልና የግል ህይወቷን በጥበባዊ መንገድ የሚያመለክቱ ሰውነታቸውን በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ ሴቶች፣ ባህላዊ አልባሳትና ቁሳቁሶች ላይ ባተኮሩት የፎቶ ስራዎቿ አለማቀፍ ተቀባይነትና እውቅና ያገኘች ባለሙያ ነች፡፡

አይዳ የልጅነት ጊዜዋን በየመን፣ እንግሊዝ፣ ቆጵሮስ፣ ካናዳና አሜሪካ ያሳለፈች ሲሆን የፎቶ ጋዜጠኝነትን ከሀዋርድ ዩኒቨርስቲ ተምራ ከአስር አመታት በፊት ወደ ትውልድ አገሯ ኢትዮጵያ ተመልሳለች፡፡

ምንጭ፡- ዘ ኒዮርክ ታይምስ