የከተሞች መድረክ ለከተሜነት

አዘጋጅ፡- ሐና ግርማ

አርታኢ፡- ሰኢድ ዓለሙ

ከ100 ሚሊዮን እንደሚልቅ ከሚገመተው የኢትዮጵያ ህዝብ 16 በመቶው ያህሉ የሚኖረው በከተሞች አካባቢ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

እነዚህ ከተሞች ደግሞ በመሰረት ልማት፣ በኢንዱስትሪና በቴክኖሎጂ ከገጠሩ የተሻለ ተደራሽነት ስላላቸው የአብዛኛው ምጣኔ ሀብታቸው መሰረት በአገልግሎት ዘርፉ ላይ እንዲመሰረት አድርጎታል።

በዚህም በገጠር ያለው ስራ አጥነትና በከተሞች ያለው የኮንስትራክሽንና የአገልግሎት ዘርፉ ማደግና መስፋፋት ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰውን ነዋሪ ቁጥር እንዲጨምር ያደርገዋል።ይህም ከተሞች አዲስ አበባና የክልል ዋና ዋና ከተሞችን ጨሮ በአሁኑ ጊዜ ፈጣን እድገትና ልማት እንዲኖራቸው ሁኔታዎች በማስገደዳቸው የከተሞች ልማት ከገጠር ጋር በተቀናጀ መልኩ ተጣጥሞ እንዲሄድ ለማድረግ በመንግስት በኩል የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተነድፈው አየተተገብሩ ይገኛል።

የከተሞች ሳምንት ጥንስስ

"የኢትዮጵያ የከተሞች ሳምንት" በሚል የተጀመረው የከተሞች ክብረ በዓልም ከዘጠኝ አመት በፊት በሚሊኒየሙ መባቻ መከበር ሲጀምርም ያለምክንያት አልነበረም። ከተሞች በመልካም አስተዳደር፣በመሰረተ ልማት ግንባታ ፣ በቤቶች ልማት፣ በስራ ዕድል ፈጠራና ቤሌሎችም የልማት ዘርፎች ምርጥ ተሞክሯቸውን እዲለዋወጡ በማደርግ የዘረፉን እድገት ተፎካካሪ በማድረግ የተፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ለማረግ በማለም ነበር። 

በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የከተሞች መድረክ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሚያዘጋጀው የከተሞች ፎረም ላይ እስከ ኮሎምቢያው መድረክ ድረስ ዘልቆም ነበር። በዚህ መድረክ ኢትዮጵያ የተቀመሩ ምርጥ ተሞክሮዎቿን አቅርባ ለአለም አገራት ከተሞች እስከ ማጋራት ደርሳለች።

ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄዱት የከተማ መድረኮች አዲስ አበባ፣ ሐዋሳ፣ መቀሌ፣ አዳማ፣ ባህርዳር እና ድሬደዋ ቀዳሚዎቹን ስድስት መድረኮች አዘጋጅተዋል፡፡ በዚህም ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ፤ መልካም ተሞክሮዎችንና ልምዶችን በማስፋት፤ እንዲሁም ጠንካራ መሰረት ያለው የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር ረገድ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ ማበርከቱን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ይገልፃል፡፡

ከከተሞች ሳምንት ወደ ከተሞች ፎረም

ከተሞችን ዕርስ በርስ በማገናኘት የጀመረው መድረክ የኋላ ኋላ ጽንሰ ሃሳቡ ውይይቶች ከተካሄዱበት በኋላ የኢትዮጵያ ከተሞች ሳምንት የሚለው ስያሜው ቀርቶ አሁን የያዘውን ቅርፅና ስያሜ በመያዝ የኢትዮጵያ የከተሞች ፎረም የሚል ስያሜ አግኝቷል።

የመጀመሪያውን የከተሞች ሳምንት በ2002 ያዘጋጀችው አዲስ አበባ ስትሆን የከተሞች መድረክ የሚለውን ስያሜ ከያዘ በኃላ የመጨረሻውን መድረክ ደግሞ ድሬዳዋ በ2007 አስተናግዳለች።

 

የ7ኛው የከተሞች ፎረም አስተናጋጅ፥ ጎንደር ከተማ

ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ መከበር የጀመረው የከተሞች ፎረም ዘንድሮ ለ7ኛ ጊዜ ጎንደር ከተማ አስተናጋጅ ነች ፡፡ በበዓሉ ላይ ከ200 በላይ ከተሞች እና የተለያዩ አለም አቀፍ እንግዶችን ጨምሮ የተለያዩ ታዋቂ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የከተሞች ፎረም መዘጋጀት ከተሞች እርስ በርሳቸው እንዲማማሩ ፤እንዲደጋገፉ እንዲተባበሩና እንዲወዳደሩ እንዲሁም በከተማ ልማት የተቀመጡ ግቦች ለማሳካት ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ይገልፃል። ከተሞች በመድረኩ ላይ ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት አውደ ርዕይ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።

የሙዚቃ ኮንሰርትና አውደ ጥናቶች በመድረኩ ላይ ከሚቀርቡት ድግሶች ውስጥ ተካተዋል። ልማትን በማፋጠን ያደጉና የተለወጡ ከተሞችን የመፍጠሩ ስራ ወቅቱ ከሚጠይቀው አስተሳሰብና ትግበራ ጋር የሚራመድ በመሆኑ 7ኛው ፎረም ከተሞችን በተሻለ ደረጃ ለመለወጥ ሂደት ትኩረት መስጠቱን ነው ሚኒስቴሩ የሚገልፀው።

በዓሉ የአገሪቷ ከተሞች በጎ ገጽታቸውን በማስተዋወቅ ከኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያላቸውን አቅም የሚያስተዋውቁበትና ልምድ የሚለዋወጡበት እንደሚሆን ይጠብቃል።

ከአዲስ አባባ 725 ኪሜ፣ ከባህርዳር 175 ኪሜ እና ከሰሜን ተራራዎች ደግሞ 120 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ጎንደር ከተማ ዝግጅቷን አጠናቃ የዘንድሮውን የከተሞች መድርክ እንግዶቿን ተቀብላ በስኬት ለማጠናቀቅ ሽር ጉዷን አጠናቃለች።እንግዶችም ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች መግባት ጀምረዋል። ራሷ ጎንደር ለሌሎች ከተሞች የምታስተምራቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳላት ሰንቃ እየተበቀች ነው።

ጎንደር ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ከተመሰረችበት ጊዜ አንሰቶ የተጠነሰሱት አሻራዎቿ እስከ አሁን ድረስ ከኢትዮጵም አልፎ ከፖለቲካዊ እስከ ኪነ ህንፃ ጥበባት ድረስ በከተማ ልማት ዘርፍ አገር በቀል እውቀትን በተግባር የምታስተምር ከተማ ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል።

ከተሞችም በተለይም አገር በቀል የኪነ ህንጻ ጥበብ የሚኖረውን ዋጋ እንዴት የማንነት አሻራ ሊሆን አንደሚችልና የውጭ ጎብኝዎችን ሳይቀር ቀልብ አንበርክኮ የሚይዘውን ትምህርት በተግባር የሚቀስሙበት ይሆናል።

የመረጃ ዋቢዎች

 .የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር

. Amhara Mass Media Agency

. History Gondar City