አሳሳቢው ድርቅና ወቅታዊ ምላሹ

በሰለሞን አብርሃ

የስልጣኔ ምንጭና የሰው ዘር መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የድርቅና የረሀብ ሰለባ ሆና ቆይታለች፡፡ ችግሩን ተከትሎም በተፈጠረው የምግብ፣ የውሃና የከብት መኖ እጥረት በሺህ የሚቆጠሩ ወገኖች ህይወታቸው እንደቅጠል ረግፏል፤ ከብቶቻቸውም ከምድረ-ገጽ እንደጠፋ የታሪክ ድርሳናት ያስታውሱናል፡፡ ለዚህ ጥቁር ታሪካችን መንስኤ የተለያዩ መላምቶችና ምክንያቶች ይነሳሉ፡፡ ድርቅ አልያም ረሀብ የሚከሰተው አንድም በፈጣሪ ቁጣ አልያም ህዝቡ ነገስታቱን ባለመታዘዝ ወይም ንጉሶች የተሰጣቸውን መለኮታዊ አደራ ባለመወጣታቸው ምክንያት ከሚለው ጀምሮ በአየር መዛባት ሳቢያ እንደሚከሰት ግንዛቤ ተይዞ ነበር፡፡

የጥንቶችን ትተን ሁለት የመንግስት ስርዓት ተሻግረን ብናይ የድርቅ አደጋ ከ1950 ጀምሮ ሀገሪቷን በተደጋጋሚ ተፈታትኗል፡፡ ከ1888 እስከ 1892 ዓ.ም ባለው ጊዜ ደግሞ በሀገሪቱ ታሪክ ‹‹ክፉ ቀን›› ተብሎ የሚጠራው የድርቅ ክስተት በሰውና በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል፡፡ በተለይ በአስከፊነቱ ወደር ያልተገኘለት የ1976/77 ዓ.ም ድርቅ ሀገሪቱ የውጭ እርዳታ እንድትማፀን ያስገደደ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡

አሁን ያለው የድርቅ መንስኤ ምንድን ነው? 

የድርቅ አደጋ መንስኤው የተለያየ ቢሆንም ተያያዥ ሊባሉ የሚችሉ በርካታ ምክንያቶች ግን አሉት፡፡ የዝናብ እጥረት፣ የምድር ሙቀት መጨመር፣ የደን መጨፍጨፍ፣ በመሬት ላይ የሚፈሱ ዥረቶች መድረቅ እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ስንመለስ በተለይ የአሁኑና ከጥቂት ዓመትታት በፊት የተከሰተው የድርቅ አደጋ በአመዛኙ መንስኤው ኤልኒኖ በሚል የሚጠራው የአየር ለውጥ ቢሆንም ከዚህ በተቃራኒ ላል ኒኖ ተብሎ የሚጠራው የአየር መዛባት ለአደጋው መፈጠር የማይናቅ ተጽእኖ እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ኤልኒኖ በምስራቃዊ የፓስፊክ ውቅያኖስ ውሃ ላይ በሚፈጠር የሙቀት መጨመር የሚከሰት ነው፡፡ ይህም ሁኔታ የቀዝቃዛና ሞቃታማ የውሃ እንቅስቃሴን እንዲሁም የንፋስ አቅጣጫን ከወትሮው ከተለመደው በመቀየር በተለያዩ የአለም አካባቢዎች ያለውን እርጥበትና ደረቃማ የአየር ሁኔታ እንዲዛባ ምክንያት ይሆናል፡፡ ክስተቱም በአማካይ ከሁለት እስከ አስር ዓመት ባለው ጊዜ ሊከሰት እንደሚችል መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ኤልኒኖ አንዴ ከተከሰተ እስከ ከ12 ወራት ሊቆይ የሚችል ሲሆን አልፎ አልፎ ደግሞ ይህ ሁኔታ ወደ አመታት ሊያሻቅብ ይችላል፡፡ በአንፃሩ ላልኒኖ የአየር ለውጥ የሚፈጠረው የምስራቅ ፓስፊክ ውቅያኖስ የባህር ጠለል ከወትሮ በተለየ አማካይ ሙቀቱ ሲያንስ አልያም ሲቀዘቅዝ ነው፡፡

የድርቅ አደጋ አለም አቀፍ ማሳያዎች

የዘንድሮም የአምናም የድርቅ ክስተት የበርካታ ሀገራትን ዜጎች ቤት ያንኳኳ አሳሳቢ አለም አቀፍ ኩነት ነው፡፡ የአለም ሙቀት መጨመር ተዳምሮ በተለይ የኤልኒኖ የአየር መዛባት በአሜሪካ የካሊፎርኒያ ግዛት፣ ህንድ፣ አውስትራሊያ፣ እንግሊዝ፣ ቻይና፣ ኢንዶኔዢያና በስፔን በድርቅ አደጋው ክፉኛ ከተመቱ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የድርቅ አደጋው ሰለባ የሆኑ ሀገሮች እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ በተለይ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን ስንመለከት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሩዋንዳ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ በችግሩ በእጅጉ ክፉኛ ተጠቅተዋል፡፡

አንድ መረጃ እንደሚያመለክተው በደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ የመንና በናይጄሪያ የሚኖሩ 20 ሚሊዮን ሰዎች በድርቁና በሀገሮቹ በተፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ የረሀብ አደጋ እንደተንዣበበባቸው አስታውቆ ነበር፡፡ ከእነዚህ ሀገራት መካከል በደቡብ ሱዳን ረሀብ ተከስቷል፡፡ ሶማሊያና የመን በእዚህ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ለመውደቅ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛሉ ነው የሚባለው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም የችግሩ ተጋላጮችን ህይወት ለመታደግ የእርዳታ ጥሪ ሲያቀርብ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ እ.ኤ.አ በ2017 በአለማችን ከ70 ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎች በረሀብ ቸነፈር እንደሚመቱ ‹‹የረሀብ ቅድመ ማስጠንቀቂያ መረብ›› የሚባል አንድ አለም አቀፍ ተቋም አስታውቋል፡፡

ብሔራዊ የአደጋ ክስተት ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ እንደሚሉት ከሆነ በኢትዮጵያ የአየር መዛባት ክስተትን ተከትሎ ከጥር ወር ጀምሮ በደቡብና ደቡባዊ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች የዝናብ መቆራረጥና እጥረት ተፈጥሯል፡፡ ይህም በአካባቢው በድርቅ የተጠቁ ዜጎች ከ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ወደ 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን አድጓል፡፡ የተረጂዎቹ ቁጥር ሊጨምር የቻለውም በኦሮሚያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብና በአማራ ክልሎች በበለግ ወቅት የተጠበቀው ዝናብ ባለመዝነቡና ባለፈው የመኸር ወቅት በተዘሩ ሰብሎች ላይ የውርጭ ወረርሽኝ ጉዳት በማድረሱ ምክንያት ነው፡፡

ኮሚሽኑ ችግሩን ለመቀልበስም በዘንድሮ በጀት ዓመት ከሚያዚያ እስከ ሰኔ ድረስ ለ2 ሚሊዮን 68 ሺህ ለሚደርሱ ተጨማሪ የድርቅ ተጎጂዎች የዕለት እርዳታ የሚውል ተጨማሪ 432 ሺህ 515 ሜትሪክ ቶን እህል፣ አልሚ ምግብ፣ ጥራጥሬና ዘይት ድጋፍ የሚያደርገው ከመጠባበቂያ የምግብ ክምችት በመውሰድ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም ምግቦቹን እያሰራጨ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ድርቁ የምግብና የውሃ እጥረት እንዲሁም የከብቶች መኖ አቅርቦት እንዲጓደል በማድረጉ መንግስት በዘረጋው የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ስርዓት በመጠቀም ችግሩን ለመቋቋም በርካታ አስፈላጊ እርምጃዎች እየተወሰደ ነው፡፡ በዚህ ረገድም ድርቁ በተባባሰባቸው በኦሮሚያ ክልል በቦረና፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ጉጂና ባሌ ዞኖች በሁለት ዙር 260 ሺህ እስር የእንስሳ መኖ ሳር መከፋፈሉን እንዲሁም በደቡብ ክልል ለጋሞጎፋ የሰገን ህዝቦች ዞን በአጠቃላይ 40 ሺህ እስር የእንስሳት መኖ ሳር መዳረሱ ተጠቃሽ ነው፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ሶማሌና በአፋር ክልሎች መስኖ መሰረት ያደረገ የእንስሳት መኖ ልማት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ድርቅ ሲከሰት ችግሩን ለመቋቋም ብሎም ለዜጎች ቀድሞ ለመድረስ መንግስት ሃላፊነት አለበት፡፡ የተረጂዎችን ህይወት ለመታደግ መንግስት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት በበለጠ የአንበሳውን ድርሻ በመያዝ በየወሩ ምግብና ምግብ ነክ የዕለት እርዳታ ሳይቆራረጥ እየሰጠ ስለሚገኝ አምናም ሆነ ዘንድሮ በተፈጠረው ተመሳሳይ ችግር የአንድም ሰው ህይወት ሳይቀጠፍ አደጋውን በመቋቋም ላይ ይገኛል፡፡

ሀገሪቱ በዚህ ስራዋ በአለም አቀፍ ደረጃ አድናቆት ተችሯታል፡፡ አደጋውን በመቋቋምና ምላሽ በመስጠት ረገድ ደግሞ ያላትን ተሞክሮ ለአለም አካፍላለች፡፡ የከብቶችን ህይወት ለማትረፍ ከመኖ አቅርቦት በዘለለ የጤና ክብካቤ ስራዎች እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ይሁን እንጂ ለድርቅ አደጋው አፋጣኝ ምላሽ ከማግኘት አንፃር አለም አቀፍ የረድኤት ተቋማትና ሀገራት ያላቸው ሚና አናሳ መሆኑን ኮሚሽኑ እንዲህ ይገልፁታል ‹‹መንግስት የድርቅ አደጋውን ለመቋቋም በያዝነው ዓመት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል አንድ ቢሊዮን ብር ሲመድብ 948 ሚሊዮን ዶላር የውጭ የእርዳታ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ሆኖም በደቡብ ሱዳን፣ ሶሪያና የመን በመሰሉ የአለም ሀገራት ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው ሰብዓዊ ድጋፍ መሰጠት በማስፈለጉ የለጋሾች ሚና ተቀዛቅዟል፡፡ ይህም በመሆኑ 92 ሚሊዮን ዶላር ከአለም አቀፍ የረድኤት ተቋማት እና አንድ ሚሊዮን ዶላር ደግሞ በአለም ምግብ ፕሮግራም በኩል ከሳውዲ አረቢያ እርዳታ ተገኝቷል››፡፡

ምንም እንኳን ዓለም አቀፍ የረድኤት ተቋማትና ሀገራት ሚና አናሳ ቢሆንም እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ የማይናቅና በርካታ ገንዘብ እያፈሰሱ በመሆኑ ይበል የሚያስብል ነው ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡ ሆኖም የተከሰተው የድርቅ አደጋ ሰፊ አካባቢን ያካለለ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ ያጠቃ እንዲሁም ቀጣይነት ሊኖረው የሚችል በመሆኑ ችግሩ አሳሳቢ ነው ቢባል የተጋነነ አይደለም፡፡ ስለሆነም በራስ አቅም መንግስት የሚከውነው የእርዳታ አቅርቦት ስራ ስኬታማ ቢሆንም የውጪ የረድኤት ተቋማትና የአለም ሀገራት ድጋፍ ሊጠናከር ይገባል ባይ ናቸው አቶ ምትኩ፡፡

ከመንግስት በተጨማሪ የእርስ በእርስ የመረዳዳት ባህላችን እዚህ ጋር ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ የግል ባለሀብቶችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደየአቅማቸው ለተጎጂ ወገኖች የሚያበረክቱት ድጋፍ የሚያበረታታ ነው፡፡ ክልል ለክልል የተደረጉ የእርዳታ ልገሳዎችም እንደዚሁ ይበል የሚያሰኙ ናቸው፡፡ በተለይ በዚህ ዓመት የአማራ ክልል ለሶማሊያና ለኦሮሚያ፣ የትግራይ ክልል ለኦሮሚያና ለሶማሊያ እንዲሁም የአፋር ክልል ለሶማሊያ ክልል የእርዳታ አቅርቦት ሰጥተዋል፡፡ ይህ በክልሎች መካከል ያለ የመደጋገፍ ባህል በህዝብ ውስጥ ፍቅር፣ መተሳሰብና አንድነትን ይበልጥ ያጠናክራል ተብሎ ይታሰባል፡፡

ከኢትዮጵያ የስነ-ምህዳር አቀማመጥ ጋር ተያይዞ የድርቅ አደጋ የሚከሰተው በአየር መዛባት ሳቢያ ነው፡፡ የዘርፉ ተመራማሪዎች እንደሚሉት የድርቅ ክስተት መቼም ይኖራል፤ አደጋውንም ማስቆም አይቻልም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የአየር ንብረት ተጽእኖ እየጨመረ ስለሚሄድ ነው፡፡ ይሁንና ድርቅን ወይም ድርቅ ወደ ረሀብ እንዳይሸጋገር በቅድመ ዝግጅት ስራ መቋቋም ይቻላል ነው የሚባለው፡፡ መንግስት የሚያከናውነው ህዝብንና እንስሳትን የማዳን ስራ ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ነው ሊባል ይችላል፡፡ በተለይም ደግሞ ድርቅን በፍጥነት መቋቋም የሚችል ህብረተሰብ በመፍጠር ረገድ ርብርብ ሊደረግ ይገባል፡፡ ለዚህም ሲባል መንግስት ለግብርናው ዘርፍ በጀት ሲበጅት በርካታ ገንዘብ ለእርጥበት አልያም ለውሃ ማቀብ ስራ ፈሰስ ይደርጋል፡፡ ይህም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡

ሀገሪቱ ድርቅን የመቋቋም አቅሟ እያደገ ስለመሆኑ

በሀገሪቱ በተመዘገበው ፈጣንና ተከታታይ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ሀብት በመፈጠሩ ሀገሪቷ ድርቅን የመቋቋም አቅሟ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል፤ ረሀብም ታሪክ ሆኗል፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ሲናገሩ ‹‹በሀገሪቱ 673 ሺህ ሜትሪክ ቶን የማሽላ፣ የበቆሎና የስንዴ መጠባበቂያ የምግብ ክምችት እና ከአንድ ሚሊዮን የሚልቅ ምግብ ነክ ያልሆነ ክምችት አለ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ተጎጂ ወገኖችን ለመታደግ መንግስት 100 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ወጪ አድርጓል››፡፡

እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ድርቅን የመቋቋም አቅሟ በየጊዜው እያደገ መጥቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ያን ያህል የውጭ እርዳታን ሳትጠብቅ በዋናነት በራስ አቅም ለዜጎች እርዳታ እያቀረበች የምትገኘው፡፡ ሆኖም የአደጋው ምላሽ አቅም ከተረጂዎች ቁጥር አንፃር በየጊዜው እየተጠና ማደግ ያለበት ጉዳይ በመሆኑ ለዘርፉ እየተደረገ ያለው ልዩ ትኩረት አሁንም ተጠናክሮ ቢቀጥል መልካም ነው፡፡ በዚህ ረገድ ብሔራዊ የአደጋ ክስተት ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በሀገሪቱ አደጋ ሲከሰት ከባለድርሻ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በመቀናጀት መከላከል፣ ማቅለል፣ ዝግጁነት፣ ምላሽ መስጠት፣ ማገገምና መልሶ ማቋቋም ተብለው የሚጠሩ የማስተባበር ስራዎችን ይፈጽማል፡፡ በስራው ሂደትም ታዲያ ድርቅ ሲከሰት ኮሚሽኑ ለተጎጂ ሰዎችና ለእንስሳት ምግብና መኖ ያቀርባል፡፡

ብሔራዊ የአደጋ ክስተት ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከድርቅ አደጋ ጋር በተያያዘ ሰፊ ሃላፊነት የተጣለበት ተቋም ነው፡፡ ኮሚሽኑ በብቃትና በፍጥነት ሃላፊነቱን ሊፈጽም የሚችለው ደግሞ በየጊዜው በተዋረድ ያሉትን አደረጃጀቶችና የሰው ሀይሉን ማጠናከር እንዲሁም አሰራሩን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ እንደሆነ እሙን ነው፡፡        

የድርቅ አደጋ መፍትሄ ምንድን ነው?

በአፈጣጠሩ አዝጋሚ የአደጋ ዓይነት እንደሆነ የሚነገርለት የድርቅ ክስተት ሊገታ ባይቻል እንኳን ችግሩ ቅጽበታዊ ስላልሆነ በቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት አማካኝነትና በዘላቂ የልማት ማዕቀፍ ተቋቁሞ ማለፍ እንደሚቻል አቶ ምትኩ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል፡፡ የመስኖ ልማት፣ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራዎች፣ የውሃ አልያም የእርጥበት ማቀብ ስራዎች፣ የደን ልማት፣ አካባቢ ጥበቃ ስራዎችና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እድገት አጠናክሮ ማስቀጠል ከብዙ በጥቂቱ በማዕቀፉ የተካተቱ ስራዎች ናቸው፡፡ እነዚህንና መሰል ተግባራትን ትኩረት ሰጥቶ መስራት የድርቅ ክስተትን ለመቀልበስ አይነተኛ መፍትኤ እንደሆኑም ይታመናል፡፡

በተለይ አርብቶአደሮች በሚበዙበት ሶማሊያ ክልል ችግሩ በዘላቂነት የሚፈታው የውሃ ልማትን ማዕከል ባደረገ የመንደር ማሰባሰብ ስራ እንደሆነ ከኮሚሽኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ በፈቃደኝነት ላይ በተመሰረተ በዚህ የመንደር ማሰባሰብ ስራ ነዋሪዎች የመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተቋማት በቀላሉ እንዲሟላላቸው ይረዳል፤ የውሃ ሀብት ልማት በአግባቡ ለመከወንም እንደዚሁ ይግዛል ይባላል፡፡

አብዛኛው የግብርና ምርት የሚገኘው በአንስተኛ ማሳ በሚተዳደሩ አብቶ-አደሮች በመሆኑ መንግስትን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት በዘርፉ ልማት የሚያደርጉት ድጋፍና ተሳትፎ ሊጠናከር፣ የአስተራረስ ዘዴውም ሊዘምን ይገባል፡፡ እነዚህና መሰል እርምጃዎች ከተወሰዱ የሌሎችን እጅ ሳይጠብቅ ችግሩ በዘላቂነት መቋቋምና የሚያስከትለውንም አደጋ መቀነስ ይቻላል ማለት ነው፡፡

በበካይ ጋዝ ልቀት ሳቢያ የሚፈጠረው የአለም ሙቀት መጨመር ይብዛም ይነስም የድርቅ አደጋ ላይ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው የዘርፉ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ፡፡ ይህም በካይ ጋዝ በዋናነት የሚመነጨው ከበለፀጉ ሀገራት እንደመሆኑ እነዚህም ሀገራት የአለም ሙቀት መጨመርን ተከትሎ በተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ ለሆኑ አዳጊና ታዳጊ ሀገሮችን ለመደገፍ የገቡትን ቃል ማክበርና የአደጋውን ጉዳት ለመቀነስ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል፡፡

ዋቢ መረጃዎች

1.ብሔራዊ የአደጋ ክስተት ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን

2.እርዝ ኢክሊፕስ ድረ-ገጽ/www.eartheclipse.com/

3.ሮበርት ክሊብለር ድረ-ገጽ /www.robertscribbler.com/

4. ኦሽን ሰርቪስ ድረ-ገጽ /http://oceanservice.noaa.gov/ እና ሌሎችም ምንጮች ናቸው