በአፍሪካ የመጀመሪያው የአለም አቀፉ "ሀይድሮ ፓወር" ጉባዔ

በአብዱልአዚዝ ዩሱፍ

ኢትዮጵያ የ2017 የዓለም ሀይድሮ ፓወር ጉባኤን ከግንቦት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለሶስት ቀናት ታስተናግዳለች፡፡  

የዘንድሮው ጉባዔ "እየተለወጠ በመጣው ዓለም የሃይድሮ ፓወርን ድርሻ ማሳደግ" በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚከበር ተገልጿል፡፡

ጉባዔው  በአለም አቀፉ ሀይድሮ ፓወር ማህበር (International Hydropower Association) አዘጋጅነት የሚካሄድ ነው፡፡

በአፍሪካ አህጉር ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው በዚሁ ጉባዔ ላይ ከ80 አባል አገራት የተውጣጡ መሪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችን ጨምሮ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ከ100 በላይ አለም አቀፍ ድርጅቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በቀጣይ 10 አመታት የሀይድሮ ፓወር ልማትና አስተዳደር ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚመክረው 6ተኛው አለም አቀፍ የሀይድሮ ፓወር ጉባኤ ከግንቦት 1­-3 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ ደምቆ ይሰነብታል፡፡

ጉባዔው በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመካሄዱ ባሻገር  በታዳሽ ሀይል ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማከናወን ላይ በምትገኘው ኢትዮጵያ መካሄዱ  ከዚህ ቀደም ከተደረጉ ጉባዔዎች ለየት እንዲል አድርጎታል፡፡

የአለም አቀፉ ሀይድሮ ፓወር ማህበር (IHA) ዳራ

(IHA) በሚል ምህጻረ ቃል በሚታወቀው የአለም አቀፉ ሀይድሮ ፓወር ማህበር (International Hydropower Association) ከ80 በላይ አገራትና ከ100 በላይ በኤሌክትሪክ ማመንጨት፣ ማስተዳደር፣ ኢንጂነሪንግና ተመሳሳይ ዘርፋች የተሰማሩ ድርጅቶችን አቅፏል፡፡

ታዳሽ ሃይልን አቅም መገንባትና ልምድ ልውውጦችን በማጠናከር ዘላቂ ሀይድሮ ፓወር ልማትን ማሳደግ የማህበሩ ዋና አላማ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ማህበሩ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እና የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች ላይ መፍትሄ የማፈላለግ ስራም ይሰራል፡፡

እአአ በ1995 በዩኒስኮ ጥላ ስር የተቋቋመው የአለም አቀፉ ሀይድሮ ፓወር ዋና መቀመጫው እንግሊዝ ለንደን ይገኛል፡፡ ደቡብ አሜሪካና ቻይና  የማህበሩ ቅርንጫፎች ፅ/ቤቶች ይገኛሉ፡፡

ይህ  ትላልቅ የሀይድሮ ፓወርን የተመለከቱ ውሳኔዎች የሚተላለፉባቸው አለም አቀፍ ጉባዔ መካሄድ የጀመረው እ.አ.አ ከ2007 ጀምሮ ነው፡፡ጉባኤውንም  በየሁለት አመቱ አካሄዷል፡፡

እስካሁን ድረስ አምስት ጉባዔዎች የተካሄዱ ሲሆን የመጀመሪያው በ1999 ዓ.ም በቱርክ ሲካሄድ ቀሪዎቹ እንደቅድም ተከታለቸው አይስላንድ (2001 ዓ.ም)፣ ብራዚል (2003 ዓ.ም)፣ ማሌዥያ (2005 ዓ.ም) እንዲሁም የመጨረሻው ቻይና (2007 ዓ.ም) ተካሄደዋል፡፡

ማህበሩ 6ተኛ አለም አቀፍ ጉባዔውን በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ከግንቦት 1፣ 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት እንደሚያካሄድ አሳውቋል፡፡

ለምን አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ)?

የአለም አቀፉ ሀይድሮፓወር ለምን አዲስ አበባ "Why Addis Ababa?" በሚል ርዕስ በድረ ገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ አዲስ አበባ የታጨችበትን ሶስት ምክንያቶች አብራርቷል፡፡

ኢትዮጵያ የመንግስታቱ ድርጅቶችን ጨምሮ በመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና የአፍሪካ ህብረት የመሳሰሉ ቁልፍ ተቋማትን ጨምሮ የ120 አገራት ኢንባሲዎችና ቁንጽላዎች መቀመጫ መሆኗን ፤ የከተማይቱ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከልነት በዘርፉ ከሚትታወቀው ከዋሽንግተን ዲሲ ከተማ  ብዙም ያልራቀ በመሆኑ አዲስ አባባ ለአለም አቀፉ ሀይድሮ ፓወር ጉባዔ ተማራጭ  መሆኗን ተገልጿል፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ፈጣን ዕደገቷን ተከትሎ የተገናባው የባቡር ፕሮጀክት ነው፡፡ አዲስ አበባ ከሰሃራ በታች ካሉ ከተማዎች በፍጥነት በማደግ ላይ ያለች ከተማ መሆኗን የገለጸው የማህበሩ መረጃ ይህንኑ ተከትሎ ከተማይቱ የትራንስፖርት ከተለመደው አየር በካይ ስርዓት ለመላቀቅ እየሰራች መሆኗ ነው፡፡

በዚህም መሰረት አዲስ አበባ በየቀኑ 200 ሺህ ሰዎችን ማጓጓዝ የሚችሉ የኤሌክትሪክ ባቡሮችን መገንባቷ በአለም ከሚገኙ ጥቂት ከተማዎች ተርታ ያስመድባታል ይላል በአለም ሀይድሮ ፓወር ማህበር በድረ ገጹ ያሰፈረው ጽሁፍ፡፡

ሶስተኛው ምክንያት ኢትዮጵያ ዕምቅ ሀይድሮፓወር አቅም ያላት አገር መሆኗ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በጠቅላላ ካላት 60 ሺህ ሜጋ ዋት የታዳሽ ሀይል አቅም 75 በመቶው ከሀይድሮ ፓወር የሚገኝ መሆኑን መረጃው ያመለክታል፡፡ አገሪቱ ያላትን የሀይድሮ ፓወር አቅም በማልማት የአከባቢው የታዳሽ ሃይል ማዕከል ለመሆን የምታደርገው ጥረት ለጉባዔው ተማራጭ አድርጓታል ፡፡

የሀይድሮፓወር አለም አቀፋዊ ሁኔታ                    

ሀይድሮፓወር የአለም አቀፍ የታዳሽ ኤሌክትሪክ ሃይልን አንበሳ ድርሻ መያዙን የአለም አቀፉ ኢነርጂ ተቋም መረጃ ያመለክታል፡፡

ከሀይድሮ ፓወር የሚገኘው ሃይል የአለምን 71 በመቶ የታዳሽ ኤሌክትሪክ ድርሻ ሲይዝ የጠቅላላ ኤሌክትሪክ ፍጆታን ደግሞ 16 ነጥብ 4 በመቶ ብቻ ይይዛል፡፡ የአለም አቀፉ የሀይድሮ ፓወር የማመንጨት አቅም 1 ነጥብ 21 ቢሊዮን ሜጋ ዋት እንደሚገመት ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

እአአ እስከ 2016 በአለም 1 ነጥብ 064 ሚሊዮን ሜጋ ዋት ሃይልን ከሀይድሮ ፓወር ማመንጨት ተችሏል ይላል የአለም አቀፉ ኢነርጂ ተቋም መረጃ፡፡

እአአ እስከ 2015 በተገኘው መረጃ በሀይድሮ ፓወር ማመንጨት አቅም ቻይና መሪነቱን ሲትይዝ አሜሪካ፣ ብራዚል፣ ካናዳ፣ ህንድና ሩስያ እንደየቅደም ተከተላቸው ተከታዩን ስፍራ ይዛሉ፡፡

አፍሪካ ሌላዋ የሀይድሮ ፓወር ዕምቅ አቅም ያላት አገር ብትሆንም ጥቅም ላይ የዋለው በጣም አነስተኛ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት መረጃ ያመለክታል፡፡ በአፍሪካ ከሚገኘው 300 ሺህ ሜጋ ዋት የሀይድሮ ፓወር ዕምቅ ሃይል መጠቀም የቻለችው 8 በመቶውን ብቻ ነው፡፡

በአፍሪካ ኢትዮጵያ 2 ሺህ 552 ሜጋ ዋት በማመንጨት ቀዳሚ ስትሆን ኮንጎ (2 ሺህ 495)፣ ዛምቢያ (2ሺህ 272) እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ (2 ሺህ 251) ሜጋ ዋት በማመንጨት ተከታዩን ስፍራ ይዘዋል፡፡

ኢትዮጵያና ሀይድሮ ፓወር

ኢትዮጵያ "የአፍሪካ የውሃ ማማ" የሚል መጠሪያን ያጎናፀፏትና ከከፍተኛ ቦታዎች ወደ ዝቅተኛ ቦታዎች የሚፈሱ ወንዞቿን ጥቅም ላይ ለማዋል ለረጅም ጊዜ ስታልም መቆየቷን "Ethiopia opens Africa's tallest dam" በሚል ርዕስ ያስነበበው ዘ ኢኮኖሚስት በተለይ በኦሞ ወንዝ ላይ የተገነባው የጊቤ lll የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብና ታላቁ የህዳሴ ግድብ በሃይል አማራጭነታቸው ሃገሪቷን ከፍተኛ ደረጃ ላይ በማድረስ ግዙፍ የታዳሽ ሃይል ኤሌክትሪክ አቅራቢ እንደሚያደርጓት ያትታል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የሀይድሮ ፓወር አቅም ካላቸው አገራት ተርታ እንድትመደብ ያስቻላት 45 ሺህ ሜጋ ዋት የሀይድሮ ፓወር ማመንጨት የሚያስችል እምቅ አቅሟ ነው ይላል  የአለም አቀፉ ኢነርጂ ተቋም መረጃ ፡፡ አገሪቱ 80 በመቶ ያህል የኤሌክትሪክ ሃይል ፍጆታዋን የምትሸፍነው ከሀይድሮ ፓወር ምንጭ በሚገኝ ሃይል ነው፡፡

አገሪቱ እያስመዘገበች ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚጠይቀውን ተጨማሪ የሃይል ፍላጎት በተጨማሪ በአከባቢው የታዳሽ ሃይል ማዕከል ለመሆን ያላትን ውጥን ለማሳካት ባላት ዕምቅ የሀይድሮ ፓወር ላይ ኢንቨስት እያደረገች መሆኗን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

እንደ ኮርፖሬሽኑ መረጃ የአገሪቱ የሃይል ፍላጎት በየአመቱ 12 ነጥብ 7 በመቶ ያድጋል፡፡ የአከባቢው አገራት የሃይል ፍላጎት ጥያቄም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ለዚህም በአገሪቱ በርካታ የሀይድሮ ፓወርን ጨምሮ የታዳሽ ሃይል ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ተገንብተው ሥራ ላይ ከዋሉት 7 የሀይድሮ ፓወር ማመንጫ ጣቢያዎች መካከል የግልገል ጊቤ 1ኛ (180 ሜጋ ዋት)፣ የጢስ ዓባይ 2ኛ (73 ሜጋ ዋት)፣ የተከዜ ኃይል ማመንጫ (300 ሜጋ ዋት)፣ የግልገል ግቤ II (420 ሜጋ ዋት)፣ የበለስ ኃይል ማመንጫ (460 ሜጋ ዋት) እና የፊንጫ አመርቲ ነሼ ኃይል ማመንጫ (97 ሜጋ ዋት) እንዲሁም በሙሉ አቅሙ ሃይል የማመንጨት ያልጀመረው ጊቤ ሶስት (1 ሺህ 870 ሜጋ ዋት) ጨምሮ ግንባታው የተጋመሰው ታላቁ የህዳሴ ግድብ (6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት) የአገሪቱን የሀይድሮ ፓወር አቅም በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድጉ ይጠበቃል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ከሀይድሮ ፓወር ብቻ ተጨማሪ 3 ሺህ 900 ሜጋ ዋት ለማመንጨት ዕቅድ መያዙን የአለም አቀፉ ሀይድሮ ፓወር ማህበር መረጃ ያመለክታል፡፡

በዕቅድ ዘመኑ ገናሌ ደዋ 3 (254 ሜጋ ዋት)፣ ገባ 1 እና 2 (385 ሜጋ ዋት)፣ ጊቤ 4 (2 ሺህ ሜጋ ዋት)፣ ጊቤ 5 (600 ሜጋ ዋት)፣ ላይኛው ዳቡስ (328 ሜጋ ዋት) እንዲሁም ሃለሌ ወራቤሳ (436 ሜጋ ዋት) ፕሮጀክቶችን ለመገንባት መታቀዱን መረጃው ያመለክታል፡፡

አገሪቱ በታዳሽ ሃይሎች ላይ የምታካሄዳቸው ኢንቨስትመንቶች የአከባቢው የታዳሽ ሃይል ማዕከል ለመሆን  ውጥና እየሰራችና በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ መሆኗን ያረጋግጣል፡፡

በኢትዮጵያ የሚካሄደው 6ተኛው አለም አቀፍ የሀይድሮ ፓወር ጉባኤ በቀጣይ 10 አመታት የሚከናወኑ የሀይድሮ ፓወር ፕሮጀክቶችና አስተዳደራቸው ላይ ትኩረት አድርጎ የሚመክረው ጉባዔ ለታዳጊ አገራት ትልቅ ዜና ነው፡፡ በተለይም በአካቢቢው የታዳሽ ሃይል ማዕከል ለመሆን እየሰራች ላለችው ኢትዮጵያ ጉባዔው ልዩ ትርጉም አለው፡፡

በተጨማሪም ኮንፍረንሱ በአፍሪካ የመጀመሪያውና የአዲስ አበባችንን ዲፕሎማሲያዊ ማዕከልነት ዳግም የሚያጎላ በመሆኑ ለአገራዊ ገጽታችን ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ በባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊቸረው ይገባል፡፡ 

 

3