የሩብ ምዕተ አመት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብታዊ ከፍታና ተግዳሮት

 

በታደሰ ሚዛን

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት ባለፉት 26 ዓመታት ኢትዮጵያን እንደ አገር ሲመራ ከነበረችበት የድህነት አዘቅት ወጥታ ወደተሻለ ምዕራፍ እንዲትሸጋገር ማድርግ ዋነኛ ግቡ አድርጎ ነበር የተነሳው፡፡ለዚህም አመችነት ለመፍጠር ሲባል ከፖለቲካዊ እስከ ኢኮኖሚ፣ ከማህበራዊ ዘርፍ እስከ መሰረተ ልማትና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ድረስ ለውጥ መምጣት እንዳለባቸው የተተለሙ መነሻዎች ነበሩ፡፡

መንግስት እስከ 1990ዎቹ መግቢያ ድረስ ጭላንጭል የታየበት እድገትን  እንደ አገር ቢያስመዘግብም ህዝብን ያረካ ሆኖ አልተገኘም፡፡

ለዚህም ሲባል በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት አዲስ አቅጣጫ መዘርጋት እንዳለበት በመረዳቱ ራሱን ለለውጥ አዘጋጅቶ ወደ ስራ ከገባ በኃላ ሰፊ መሰረት ያለው ለውጥ በተለይም ሁሉን አቀፍ ምጣኔ ሀብታዊ የእድገት አቅጣጫ እውን አድርጓል፡፡

ተሃድሶ የወለደው የኢኮኖሚ ዕምርታዊ ለውጥ

የኢፌዲሪ መንግስትን ይመራ የነበረው ኢህአዴግ ከ1997ቱ ምርጫ በኃላ ህዝብ ያነሳው ከነበራቸው ለውጦችና መሻሻሎች መካከል የኢኮኖሚ እድገትና ፍትሃዊ የሀብት ተጠቃሚነት ከሚነሱ ህዝባዊ አጀንዳዎች መካከል ይገኙበታል፡፡ ኢህአዴግ የሚመራው የኢፌዲሪ መንግስትም ህዝቡ ከሚያነሳቸው ጥያቄዎች መካከል ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ጎልተው በመውጣታቸው የህዝቡን የማደግና የመለወጥ ፍላጎት  በመረዳት ራሱን ወደ ተሃድሶ ጉዞ በማስገባት ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ አገሪቱን ወደ አዲስ መንገድ እንድትገባ አድርጓል፡፡ በዚህም ለግብርናውና ለኢንዱስሪው ዘርፍ ትኩረት በመስጠት ስራ አጥነትን መቀነስና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት ያደረገው የግብርና መር ኢኮኖሚ ስርዓት ተከታታይ እድገት እንዲመዘገብ በር የከፈተ የተሃድሶ ምዕራፍ ነበር ሆኖ ያለፈው፡፡

ከቀዳማይ ተሃድሶ በኃላ ህዝቡን በዋና ዋና ጉዳዮች ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት እንዲደርስ ማድረጉ የኢኮኖሚያዊ እድገቱን ስኬታማ እንዳደረገውም ነው የሚታሰበው፡፡

የኃላ ኃላ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት  ቀጣይነት ለማረጋገጥ መንግስት ሁለት ተከታታይነት ያላቸውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ነድፎ ወደ ስራ እስከማግባትም ደርሷል፡፡

ኢትዮጵያ ከቀዳማይ ተሃድሶ በኃላ አገሪቱ ግብርና መር የነበረውን  የምጣኔ ሀብት ፖሊሲዋን  ወደ ኢንዱስትሪ መር እስከ መቀየር የተደረሰችው የህዝቡንና የአገሪቱን የእድገት አቅጣጫ ከወቅታዊና አለማቀፋዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ለማጣጣም ነው፡፡ 

ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶችን ለቀጣይ የብሔራዊ መግባባትና የገፅታ ግንባታ ስራዎቻችን መጠቀም ተገቢ መሆኑን ብዙዎች ይመክራሉ፡፡ አገራዊ እቅድ ሆነው ያልተከወኑ ካልተከናወኑ ስራዎች ጋር በተያያዘ ፈታኝ በነበሩ ችግሮች ዙሪያ ህብረተሰቡን መግባባት ላይ በማድረስ ለቀጣይ ስራዎች ህዝባዊ ንቅናቄ ለመፍጠር የሚያግዝ መነሻ ማስቀመጥም ወሳኝ መሆኑንም የፖላቲካ ኢኮኖሚ ጠበብቶች ይመክራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት፤  በየበጀት ዓመቱ በአማካይ በለ ሁለት አሀዝ ሁኖ ለበርካታ አመታት ማደጉ ለሌሎች አገራትም ጭምር በተምሳሌትነት የምትጠቀስ አገር አድርጓታል፡፡ የተመዘገበው ምጣኔ-ሃብታዊ ዕድገትም በሀገር ውስጥም  ሆነ በውጪው ዓለም እውቅናና ተቀባይነት ያገኘ ከመሆኑም በተጨማሪ ኢትዮጵያ በተከታታይ ፈጣን ዕድገት ከሚያስመዘግቡ ጥቂት የዓለም ሀገራት መካከል እንዲትሆን ያስቻለ ነው። ይህ ስኬት ኢትዮጵያን በየደረጃው የሚያጋጥማትን ፈተናዎች በማሸናፍ የተያዙ ትልሞችን ማሳካት እንደምትችል ተጨባጭ ማስረጃ ሆኗል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና

ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት በተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት የግብርና ዘርፉ ምርታማነት ማደግ ከፍተኛ ድርሻ አበርክቷል። በዚህ ሂደት ፤ የኢትዮጵያውያን ምጣኔ ሃብታዊ የህዝብ ንቅናቄ ድጋፍ በመፍጠር ረገድ ህዝቡ የማይተካ ሚና ተጫውቷል።

በቀዳሚነት ዋናው የዘርፉ የዕድገት ምንጭ በዋናነት የአርሶ አደሩና የአርብቶ አደሩ ግብርና ወሳኙን ሚና እንደሚጫወቱና በተጨማሪም በግል ባለሃብቱ የሚካሄደው የአበባ ፣አትክልትና ፍራፍሬ  ሰፋፊ እርሻዎች ልማቶችም የበኩላቸውን ሚና የተወጡ መሆናቸውን ከማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በዚህም መሰረት ባለፉት ዓመታት በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ፈጣንና ዘላቂ የግብርና ልማት ሊያረጋግጡ የሚችሉ በርካታ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በዚህም በየዓመቱ በአማካይ 6.6 በመቶ የግብርና ተጨማሪ ዕሴት ዕድገት ለማስመዝገብ ተችሏል፡፡ የተመዘገበው የግብርና ተጨማሪ ዕሴት ዕድገት በብዙ መለኪያዎች ፈጣን ቢሆንም  ከተቀመጠው የ8.6 በመቶ ዓመታዊ አማካይ ግብ አንፃር በመጠኑ ዝቅ ማለቱን ሪፖርቶች ያመላክታሉ፡፡

እንዲህም ሆኖ ይህን ዓመታዊ ግብ ለማሳካትም በተደረገው ርብርብ ፤ የአነስተኛ አርሶ አደሮች የመኸር ሰብል ምርት ለማሳደግ በተደረገው ጥረት ለአብነት፤ በ2002 ከነበረበት 180 ሚልዮን ኩንታል በ2007 ወደ 270.3 ሚሊዮን ኩንታል በማደግ የ90 ሚሊዮን ኩንታል ጭማሪ ለማስመዝገብ ተችሏል፡፡ የምርት አፈፃፀሙ መሠረታዊ የዕድገት አማራጩን ያሟላ እና አገራችን በምግብ ሰብል ራሷን እንድትችል ያስቻለም መሆኑን ነው የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የሚገልፀው፡፡  በገጠርም በከተማም የሚገኘው እያንዳንዱ ዜጋ ይህንኑ ምርት ገዝቶ መጠቀም የሚያስችለው የመግዛት አቅም እንዲያዳብር ለማድረግ የሚያስችሉ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎችም  በስፋት እየተከናወኑ ናቸው፡፡

መዋቅራዊ ሽግግሩን እንዲመራ የታለመለት የአትዮጵያ ኢንዳስትሪ

ባለፉት 25 ዓመታት ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዘርፍ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፋለች፡፡ በተለይም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት የንግድ ሚዛኑን ለማስተካከልና የስራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ቁልፍ ሚና ተጥሎበት ነበር፡፡በተለይ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መዋቅራዊ ለውጡን ከግብርናው ተረክቦ እንዲመራ ከፍተኛ ኃላፊነትም ተሰጥቶታል፡፡ በ1980ዎቹ በጣት ይቆጠሩ የነበሩ ፋብሪካዎች አሁን ላይ በመላ አገሪቱ እንደ አሸን እንዲፈሉ አድርጎታል፡፡

በተለይም በየአመቱ በርካታ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመሳብ የተሰራው ስራ አሁን ላይ እየተገኘ ላለው የዘርፉ እድገት አስተዋፅኦው እንዲጎላ አድርጎታል፡፡

እንደ ቻይና ቱርክ፣ህንድ፣ሳውዲ አረቢያና ሌሎች አገራትም በበርካታ የኢንዱስትሪ ዘርፎች  ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የልማት አጋር እስከ መሆን ደርሰዋል፡፡

ለዚህ ጥረት የአገሪቱ ስኬታማ የሆነው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ወሳኙን ሚና ተወጥቷል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሪፖርት እንደሚያሳየው ባለፉት አምስት ዓመታት የኢንዱስትሪ ዘርፍ በየዓመቱ በአማካይ 20 በመቶ አድጓል፡፡ ከታቀደው የዕድገት ምጣኔ አኳያ የተሳካ ዕድገት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመካከለኛና ትላልቅ አምራች ኢንዱስትሪ 19.2 በመቶ እና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪ 4.1 በመቶ ዓመታዊ አማካይ ዕድገት አስመዝግበዋል፡፡ ለአብነት በ2007 የበጀት ዓመት የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት የነበረው ድርሻ 15.1 በመቶ ለማሳካት ቢቻልም በሚፈለገው መጠን ተጉዟል ማለት ግን አይቻልም፡፡

ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት የስራ ፈጠራ ክህሎት መስፋፋት፣ የቴክኖሎጂና የክህሎት፣ የካፒታልና የገበያ ችግሮች ለማቃለል፤  በተደረገው እንቅስቃሴ በመላ አገሪቱ በርካታ ተቋማትን ለማስፋፋትና የሥራ ዕድል ለመፍጠር ተችሏል፡፡ ሥራው በተሻለ ሁኔታ በተከናወነባቸው አካባቢዎችም የኢንተርኘሪነርሺኘ አስተሳሰብ መጐልበት፣ የንግድና ኢንቨስትመንት መነቃቃት እና የሥራ አጥነት መቀነስ ታይቷል፡፡

ከዚህ አንፃር በቀጣይ የሚደራጁት ኢንተርኘራይዞች በዋናነት በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ላይ የተሠማሩ መሆን እንዳለባቸው አመላካች ነው፡፡

እንደ ማጠቃለያ

አሁንም ቢሆን በግብርናና በኢንዱስትሪ ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ለውጥ ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ይፈለጋል፡፡

አገሪቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የማህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በተሰራው ስራ  የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ባለፉት 25 ዓመታት ከሰባት እጥፍ በላይ ጨምሯል።

የአንድን አገር የነፍስ ወከፍ ገቢ ሊያሳድጉ ከሚችሉ ነገሮች በዋናነት የሚጠቀሰው ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ነው።

ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት በአገሪቱ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት አዝጋሚ በመሆኑ የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ 100 የአሜሪካ ዶላር እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚህም በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የነፍስ ወከፍ ገቢ 750 ዶላር ደርሷል።

የኃብት ፍትሃዊነትን ለማምጣት ህብረተሰቡ የማምረት አቅመሙን ተጠቅሞ በአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ በንቃት መሳተፉም ለገቢው መጨመር ዓቢይ ምክንያት ሆኗል።

እድገቱ የዜጎችን ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ያረጋገጠ ነው ሲባል፤ በእድገቱ በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ ስለመሆናቸውና የገቢ አቅማቸው ተሻሽሎ ድህነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ማስቻሉን የሚያመላክት ነው።

ይህ ደግሞ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ለመፍጠር የተያዘውን ራዕይ ለማሳካት የሚያስችል ነው፡

በአጠቃላይ ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት የተመዘገቡ ምጣኔ-ሃብታዊ ውጤቶችንና የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን እንዲሁም የቀጣይ  ዓመታት ግቦችን መነሻ በማድረግ ተገቢና የተመጋገቡ ምጣኔ ሃብታዊ ሃገራዊ ዕቅዶች በመንደፍና፤ የነበሩትን ስኬቶችን በማጠናከር፤ ቀጣይነት ያለው ህዝባዊ ንቅናቄ መፍጠርና በጎ ተፅዕኖ መፍጠር መቻል እንደሚጠይቅ ብዙዎች ይስማሙበታል። 

ከዚህም ባለፈ ህዝብ ላነሳቸው የተለያዩ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ያሰበው መንግስት በሁለተኛው ተሃድሶ የተነሱ የህዝብ የማደግ ፣የመልማትና የመልካም አሰተዳደር ጥያቄዎች አሁን ላይ የተመዘገበውን የምጣኔ ሀብት እድገትና ተጠቃሚነት የበለጠ ለማሳደግ ልዩ ትኩረት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡የዘንድሮው የግንቦት 20 ህዝባዊ በዓልም እነዚህን ስኬቶች ወደተሻለ ምዕራፍ ማጎልበት ላይ የበለጠ እነዲሰራ አመላካች ሆኖ መጥቷል፡፡