ድንበር ተሻጋሪ ሰብዕና

ድንበር ተሻጋሪ ሰብዕና

በበክሪ ናስር

                                                                                                                    
  1. መለስ በህዝቦቹ ጥቅም የማይደራደር ነበር 

ፖል ካጋሜ

  1. የአፍሪካ እውነተኛ ልጅ ፣ ለሀገሪቱ ያበረከተው አስተዋፅኦ ከቃላት በላይ ነው

                                ታቦ ምቤኪ                                                   

  1. የምርጥ አዕምሮ ባለቤት ፤ የኩሩ ህዝብ ኩሩ መሪ

                                ሱዛን አልዛቤት ራይስ

  1. ሁሌም የሀገሩንና የአፍሪካን ችግር አስመልክቶ የሚሰጠውን ትንታኔ መስማት ያስደስተኛል                              

                                    ባን-ኪ-ሙን

  1. የበርካታ ችግረኞችን እጣ ፈንታ ለማቃናትና ድህነትን ለመቀነስ የተጋ መሪ

                                ባራክ ኦባማ

እነዚህ የምስክርነት ሃሳቦች የቀድሞ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊን አስመልክቶ ከውጭ ሰዎች የተሰጡ ናቸው፡፡ ሀገሬው ደግሞ በየቋንቋው ከዚህ የላቀ ምስክርነት ሲሰጥ በተደጋጋሚ ይደመጣል፡፡

የኝህ ታላቅ መሪ ህልፈት 3ኛ ዓመት መታሰቢያ በሀገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በክልሎች እየታሠበ ይገኛል፡፡ ከሀገር ውጪ ባሉ የሀገሪቱ ኤምባሲዎች ይኸው የመታሰቢያ ዝግጅት የሚጠበቅ ሲሆን በሌሎች ሀገራት የመታሰቢያ ዝግጅቱ እየተካሄደ ነው፡፡

አፍሪካዊቷ ርዋንዳ ከዚህ ሃሳብ ጋር ትነሳለች -ይህች ሀገር ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊን የሚዘክር መድረክ አዘጋጅታለች፡፡ መድረኩ በአቶ መለስ የልማታዊ መንግስት አስተምህሮ ላይ ያተኮረ ሲሆን  ርዋንዳ ከአፍሪካ ልማት ባንክና ከመለስ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀችው ነው፡፡  መለስ በህይወት በነበሩበት ዘመን ለሀገር፣ ለአህጉርና ለአለም ጥለው ያለፏቸው ዘመን ተሻጋሪ አበርክቶዎች የሀገር፣ የአህጉርና የዓለም ንብረት አድርጓቸዋል፡፡ ለዚህም ነው ዓለም በጋራ እንዲያስባቸው የሆነው ፡፡

የዚህ ጽሁፍ አላማ የመለስን ረጅም ጉዞ መተንተን አይደለም ይህ ዓለም አቀፋዊ ስብዕናን እንዴት ሊገኝ እንደቻለ በጥቂቱ ለማንሳት እንጂ ፡፡ የመለስ አበርክቶዎችን በ2 ከፍለን

ስናይ፡-

  1. መለስ ለሀገሩ

አቶ መለስ ከወጣትነት እስከ ጐልማሳነት ብሎም እስከ ህልፈተ ህይወት ድረስ ያለፉባቸው መንገዶች ሀገራዊ ይዘት የነበራቸው ናቸው፡ በተማሪነት ዘመናቸው በሀገሪቱ የነበሩ ዋና ዋና ህዝባዊ ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎችን አንግበው ነበር ለትግል የተነሱት፡፡

መለስ በሀገሪቱ ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን በሁሉም የትግል አውዶች ከወታደርነት እስከ መሪነት አገልግለዋል፡፡ ከትጥቅ ትግል ወዲህ በነበሩ የ198ዐዎቹ ዓመታት የዛሬይቱን ኢትዮጵያ የወሰነ ፈተና ማለፍ የቻሉ መሪም ነበሩ፡፡

ከደርግ ውድቀት ማግስት የነበረውን ፈተና አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ ከመበታተን ድና እንደሀገር  የምትቀጥል ለማድረግ የተሄደው ርቀት ውጣ ውረድ የበዛበት እንደነበር የሚታወስ ሆኖ ይህንን ፈተና በስኬት ለማለፍ የመለስ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነበር፡፡ ይኸው አስተዋፅኦዋቸው አድጐ የሽግግር መንግስቱን መሪነት በተሳካ ግን ደግሞ በየጊዜው ብልጭ የሚሉ የቅድመ ሽግግር ወቅት ፍላጐቶች ጋር ጽናት በሚጠይቅ ትግል ውስጥ አልፈዋል፡፡

የሽግግሩ ዘመን ሀገር ከማረጋጋት ባለፈ ለቀጣይዋ ኢትዮጵያ ህገ-መንግስታዊነት መሠረት የጣለ ጊዜ ነበር፡፡ ይህ ጊዜ የህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሸን ከማቋቋም እስከ ህገ-መንግስት ማርቀቅ ሲያልፍም ማጽደቅ አይነት ሁነቶች የታዩበት እንደ መሆኑ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ላይ ቀጥተኛ አዎንታዊ ተፅዕኖ የነበረው ነው፡፡ ከዚህ ፍፃሜም ጋር በቅድሚያ የሚጠቀሱ ሰው ነበሩ - መለስ ዜናዊ፡፡

በ1987ዓ.ም አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ተካሂዶ አቶ መለስና የሚመሩት ፖርቲ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ በነበሩ የተወሰኑ አመታት ሀገሪቱን ወደ ዘላቂ መረጋጋት ከማምጣት ባለፈ ኢኮኖሚው ከገባበት አዘቅት የማውጣት ፈተና የመንግስት ሆኖ ነበር፡፡ በዚህም ጥሩ ስኬት ማስመዝገብ ተችሎ ነበር፡፡

የዚያን ወቅት መረጃዎች እንደሚያሳዩት በተለይ በ1990ዎቹ መጀመሪያ አመታት ሀገሪቱ በአፍሪካ ከፍተኛ ሊባል የሚችል የ5 በመቶ እድገት አስመዝግባ ነበር፡፡ ይህ ግን የሀገሪቱን ጥልቅ ችግሮች መፍታት የሚያስችል አቅም የነበረው አይደለም፡፡

ይህንን የተረዱት መለስ ሁሉም ዘርፍ ሀገሪቱ ለምትደርስበት ደረጃ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዲኖረው የሚያስችል ፣ መነሻውና መድረሻው የሚታወቅ ፖሊሲ ማዘጋጀት ጀመሩ፡፡

ዛሬ ዛሬ ለዓመታት ተተግብረው ውጤት እያስመዘገቡ ያሉት በኢኮኖሚው ዘርፍ የግብርና ልማት ፖሊሲና የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ በማህበራዊ ዘርፍ ደግሞ የትምህርትና የጤና ፖሊሲ እንዲሁም ለዛሬው ሃገራዊ የዲኘሎማሲ ስኬት መሠረት የሆነው የውጭ ግንኙነትና የደህንነት ፖሊሲ ከአቶ መለስ የአዕምሮ ውጤቶች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

እነዚህ ሃገራዊ ፖሊሲዎች እንደ ሰነድ በእያንዳንዳቸው ውስጥ ከያዙት የሁኔታዎች ትንተና ባለፈም አንደኛው ፖሊሲ ከሌላኛው ፖሊሲ ጋር ጥብቅ ተመጋጋቢነት እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ያሳዩት ብቃት ሰብዕናቸውን በጉልህ ያሳየ ነበር፡፡

በፖሊሲዎች ተፈፃሚነት ውስጥም የሀገሪቱ ህዝብ ቀጥተኛና ነፃ ተሳትፎ እንዲኖረው ዲሞክራሲያዊ ባህል መሠረት እንዲይዝ ተችሏል፡፡በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ኑሮአቸው እንዲለወጥ ፣ ሀብት እንዲያፈሩና የምግብ ዋስትናቸው እንዲያረጋግጡ ብቃት ያለው አመራር የሰጡ መሪ ነበሩ  - መለስ፡፡

ከተሜው በተለይ የኢንዱስትሪው ልማት ፖሊሲን መነሻ ባደረገ ሁኔታ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርኘራይዞች ልማት ላይ  በማተኮር ተመጋጋቢ እድገትና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር የሰሩ መሪም ነበሩ፡፡ በከተማ ልማት ፖሊሲው በግልፅ የተቀመጠው የከተሞችን ድህነት መቅረፍ የሚያስችሉ የቤት ልማት ኘሮጀክቶችን የመሩና የከተማውን ነዋሪ ለመጥቀም የተጉ መሪም ነበሩ፡፡

ከአሳታፊነት አንፃርም አቶ መለስ የሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎ ለማረጋገጥ የነበራቸው እምነት  የተጓዙት ርቀት ዛሬ በሀገሪቱ እየታየ ላለው የሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎ መሠረት የጣለ ነው፡፡ ያለ ሴቶችና ወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተሳትፎ ተፈላጊውን ውጤት እንደማይመዘገብ የተረዱና ለዚሁ የሰሩ መሪም ነበሩ፡፡

ከ1 ወር በፊት ውጤቱ የተገመገመውና ለአጠቃላይ ሀገራዊ ራዕይ ማሳካት ቁልፍ እንደሆነ የሚገለፀው የመጀመሪያውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሀንዲስ ከመሆን ባለፈም እስከ ህልፈት ህይወታቸው ድረስ በብቃት በመምራት ከድህነት ለመውጣት የምትታትር ሀገር አበርክተው ያለፉ መሪ ናቸው፡፡

  1. መለስ ለአፍሪካና ለአለም

አቶ መለስ በህይወት ዘመናቸው ለሀገራቸው እድገትና ለውጥ የተጉትን ያህል ለአፍሪካና ለድሀ የዓለም ሀገራት ባበረከቱት አስተዋፅኦም ይታወቃሉ፡፡ ለሀገራቸው ኢትዮጵያ እንዳደረጉት ሁሉ የአፍሪካ ሀገራት የፖሊሲ ነፃነት ኖሯቸው የራሳቸው ችግር በራሳቸው የመፍታት እድል እንዲሰጣቸው ሞግተዋል፡፡ በአፍሪካውያን ላይ የደረሰውን በደል ሊክስ የሚችል የንግድና ፋይናንስ ፓኬጅ በማዘጋጀት ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን በሚመለከት የአፍሪካውያንና የሌሎች ድሃ የዓለም ሃገራት ድምፅ እንዲሰማ ያደረጉ በአፍሪካውያን የሚከበሩ ታላቅ መሪም ነበሩ፡፡

መለስ የአፍሪካ ሠላምና አካባቢያዊ ኢኮኖሚያዊ ትብብርን በማጠናከር የአፍሪካ ህዳሴን ለማረጋገጥ የተጫወቱት ከፍተኛ ሚናም በአፍሪካውያን ልብ የሚያኖራቸው ነው፡፡ ለአፍሪካ የሠላም፣ የመልካም አስተዳደርና የልማት ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ሊፈለግ ይገባል በማለት መፍትሄዎችን በመቀየስ፣ የመፍትሄ ሃሳቦቹ ተቀባይነት እንዲኖራቸው በመንቀሳቀስ ተጨባጭ ውጤት ያስመዘገቡ መሪም ናቸው፡፡

የአፍሪካ ጥቅም የሚረጋገጠው በተበታተነ አኳኋን በሚደረግ ጥረት ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በአንድ ድምፅ የምትወከልበት ሁኔታ በመፍጠር እንደሆነ በማመንና በማሳመንም ሰርተዋል፡፡

የአፍሪካ ምርቶች በአለም ገበያ የሚኖራቸው ዋጋ እንዲጨምር ወደ አፍሪካ የሚፈሰው ኢንቨስትመንት በመጠንና በጥራት እንዲሻሻል ፣ እርዳታና ብድር እንዲያድግ ፣ የዓለም የንግድ ስርዓት ለአፍሪካ እድገት አመቺ የሚሆንበት ሁኔታ እንዲፈጠር በተለያዩ የአፍሪካና የዓለም አቀፍ መድረኮች በከፍተኛ ሁኔታ ታግለዋል፡፡

መለስ የአፍሪካ ሀገራት ያላቸውን የመልማት ዕድል ሊጐለበት የሚችለው በጠንካራ ትብብርና ትስስር በመንቀሳቀስ እንደሆነ በማመን፣ በተገቢው ትንታኔ በማስረዳት ለስኬት ተግተዋል፡፡ ሀገራት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሊያተሳሰር የሚችል በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የጋራ ልማት ሊስፋፋ ይገባዋል፤ የሚል ፅኑ እምነት ነበራቸው፡፡

በዚህም ኢትዮጵያና የአካባቢው ሀገራት በመሠረተ ልማት እንዲተሳሰሩ ፣ በአባይ ወንዝ ልማት ላይ ለዘመናት ተንሰራፍቶ የነበረው ፍትሃዊ ያልሆነ አስተሳሰብ እንዲሸረሸርና የሀገራት የጋራ ጥቅም የሚያስተባብር አተያይ የበላይነት እያገኘ እንዲመጣ ውጤታማና ታሪካዊ ስራ የሰሩ ለአፍሪካውያን የጋራ ጥቅሞች የታገሉ መሪም ነበሩ መለስ ዜናዊ፡፡

በነዚህና በሌሎች በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ባልተካተቱ አስተዋፅኦዎች ምክንያት ነው በሀገር ደረጃ የመለስን መታሰቢያ ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች እንዲታሰብ ያደረገው፡፡ ለዚህ ነው  በዚህ ጽሁፍ መግቢያ ላይ የሰፈሩት የተለያዩ ሀገራትና ተቋማት መሪዎች ምስክርነታቸውን በቃላቸው እንዲሰጡ ያደረጋቸው፡፡

ለዚህም ነው የመለስን አፍሪካዊነትና አለም አቀፋዊነት በሚያሳይ መልኩ በርዋንዳዋ ርዕሰ ከተማ ኪጋሊ የመለስ ዜናዊ 3ኛ ዓመት መታሰቢያ መድረክ የተዘጋጀው፡፡