ዳዊት ፅጌ በድምፅ፣ ኢትዮጵያዊነት የዳንስ ቡድን በውዝዋዜ የባላገሩ ምርጥ አሸናፊዎች ሆኑ

/መስከረም 17፣2008/ ዳዊት ፅጌ  በድምፅ፣ኢትዮጵያዊነት የዳንስ  ቡድን በውዝዋዜ  የባላገሩ ምርጥ አሸናፊዎች ሆኑ።

 የባላገሩ ምርጥ ከስድስቱ የድምፅና ከአምስቱ የውዝዋዜ ቡድን  ተወዳዳሪዎች አሸናፊዎቹ  ተለይተዋል።

ለሶስት ዓመታት ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ ፍፃሜውን ባገኘው  የ2008 ባላገሩ  ምርጥ የድምፅ ተወዳዳሪ አሸናፊ ዳዊት ፅጌ 1ኛ  በመውጣት የ300 ሺህ ብር ሽልማቱን ወስዷል። ዳዊት የድምፅ አሸናፊ  በመሆኑ በባለገሩ ሪከርዲስ ሙሉ አልበም ይሰራለታል።

ኢሳያስ  ታምራት    ደግሞ 2ኛ   በመሆን የ150 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶለታል። ከስድስቱ  የድምፅ ተወዳዳሪዎች ሜላት መንገሻ የሶስተኛ ደረጃን በመያዝ የ70 ሺህ ብር ተሸላሚ  ሆናለች። 

በውዝዋዜና ዳንስ ዘርፍ በነጣላና በቡድን በተካሄደው ፉክክር ደግሞ ኢትዮጵያዊነት የውዝዋዜ  ቡድን አንደኛ ሲውጣ፣ ጃቤዛ ባህላዊ  የውዝዋዜ  ቡድን ሁለተኛና ዮድ አዲስ ዘመናዊ የዳንስ ቡድን ሶስተኛ በመሆን የባላገሩ  ምርጥ አሸናፊዎች በመሆን የ300 ሺህ፣ 150ሺህና 70ሺህ ብር ሽልማት ወስደዋል።

በነጠላ ዳንስ ከቀረቡት አራት ተወዳዳሪዎች ደግሞ ያሬድ ኬኔ አሸናፊ  በመሆኑ  የ30 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶለታል።  

የባላገሩ ምርጥ አሸናፊዎቹ የተለዩት 60 በመቶ ከህዝብ  በተሰበሰበ እንዲሁም 40  በመቶው ከዳኞች በተሰጠ  ድምፅ ነው።

ላለፉት ሶስት አመታት በኢትዮጵያ  ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሲተላለፍ የነበረው የቀድሞው "የባላገሩ አይዶል" የአሁኑ ደግሞ "የባላገሩ  ምርጥ" ሾው ለአሸናፊዎቹ የዋንጫና የገንዘብ ሽልማት ከመስጠት ባሻገር አሸናፊዎቹ በባላገሩ ቁጥር 4 ይሳተፋሉ።