"ሜይ 21" የአለም አቀፉ የብዝሃነት ቀን

በአብዱልአዚዝ ዩሱፍ

በአለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰቱ ግጭቶች የሶስት አራተኛው መንስዔ ብዝሃነትን አለማስተናገድ መሆኑን የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ያመለክታል፡፡

ድርጅቱ "Why does cultural diversity matter?" በሚል ርዕስ በቅርቡ ያሰራጨው ዘገባ ብዝሃነትን ማስተናገድ ጊዜ የማይሰጠውና ለሰላም፣ መረጋጋትና ልማት መሰረት መሆኑን ይገልጻል፡፡

በተለይም ባህልን መሰረት ያደረገ ብዝሃነትን በስኬት ማስተናገድ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር አእምራዊ፣ ሞራላዊ፣ ስሜታዊ እንዲሁም መንፈሳዊ ፍላጎቶችን የማሟላት ሚናው ከፍተኛ መሆኑን የመንግስታቱ ድርጅት በየአመቱ እአአ ግንቦት 21 የሚያከብረውን የብዝሃነት ቀን አስመልክቶ ባወጣው ጽሁፍ ተብራርቷል፡፡

በተለያዩ ባህሎች መካከል መቀራረብ እንዲፈጠር ሚድያዎችን ጨምሮ ሌሎች መገናኛ ዘዴዎች ፈጠራን አክሎ መረጃዎችን ማድረስ እንደሚገባቸው ተጠይቋል፡፡

በዩኒስኮ አቅራቢነት የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ "ሜይ 21"ን ብዝሃነት ለውይይትና ለልማት (Diversity for dialogue & development) ተብሎ እንዲከበር ነው የተወሰነው፡፡

በግንቦት 20 ዋዜማ ግንቦት 13፣ 2009 ዓ.ም የሚከበረው የዘንድሮው የአለም አቀፉ የብዝሃነት ቀን፤ የብዝሃነትና የህብረ ብሄራዊነት ማዕከል ለሆነችው ኢትዮጵያ ልዩ ትርጉም ይኖረዋል፡፡

የብዝሃነት ሳይንሳዊ ዕይታ

The Ultimate Obamacare Handbook ጨምሮ በርካታ ብዝሃነትን የተመለከቱ  መጽሃፍት የጻፉት አሜሪካዊቷ ኬምበርሊ አማዶ ባህልን መሰረት ያደረገ ብዝሃነትን ውጤታማ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል ይላሉ፡፡ ልዩነቶችን በሰከነ አእምሮ መረዳትና ማስተናገድን ይጠይቃል፡፡ በተለይም ማንነትን መሰረት ያደረገ ድምዳሜ ላይ እንዳይደረስ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት የስነ-ልቦና እና የኢኮኖሚክስ ምሁሯ ኬምበርሊ አማዶ ያስጠነቅቃሉ፡፡

ልዩነቶችን በአግባቡ ማስተናገድ ከተቻለ ብዝሃነት ለአገርም ሆኑ ለኩባንያዎች የተለያዩ ልምዶችን ቀምረው ወደ ተሻለ ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬን እንደሚያጎናጽፍ ያስረዳሉ፡፡

በአለማችን ስኬታማ የሚባሉ ግዙፍ ድርጅቶች የስኬታቸው ምስጥር ብዝሃነትን ማሰተናገዳቸው መሆኑን የሚገለጹት ምሁሯ ኬምበርሊ አማዶ ጎግል፣ ጆንሰን እና ኢንቴልን ለአብነት ያነሳሉ፡፡

"ሰዎችን በማንነታቸው አትለካ" "Never judge a people by their appearance." የሚል መሪ ቃል ያለው ጉግል የአለማችን 62 በመቶ መረጃ ፈላጊዎች ይጠቀሙበታል፡፡

ከ200 አገራት የተውጣጡ ከ72 ሺህ በላይ ቋሚ ሰራተኞች ያሉት ጎግል በአለማች በሚገኙ ከ4 ሺህ ቋንቋዎች በላይ መረጃዎች ይፈለጉበታል፡፡

ጆንሰንና ኢንቴልም በመተሳሳይ ከ100 አገራት በተውጣጡ ሰራተኞች የተደራጀ አለም አቀፍና ውጤታማ ኩባንያዎች መሆናቸው ለአብነት ቀርቧል፡፡

በአንፃሩ ብዝሃነትን በተለይም ባህልን መሰረት ያደረገ ብዝሃነት ማስተናገድ ካልተቻለ አደጋውም ከፍተኛ መሆኑን ምሁሯ ያስጠነቅቃሉ፡፡

ባህልን መሰረት ያደረገ ብዝሃነት የዘር፣ የብሄር፣ የቋንቋ፣ የዜግነት፣ የሃይማኖት እና የጻታ ብዝሃነትን እንደሚያጠቃልል አሜሪካዊቷ ምሁር ኬምበርሊ አማዶ ገልጸዋል፡፡ 

ሌላው ብዝሃነትን አስመልክቶ "ህብረ-ብሄራዊ የፌዴራል ስርዓት" በሚለው ጽሁፋቸው ያብራሩት አቶ እውነቱ ብላታ ናቸው፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ ብዝሃነት በተፈጥሮ የሚገኝ፣ በዓይነት ወይም በልዩነት ላይ የተመሠረተ የቁጥር ብዙነት ብቻ አለመሆኑን የሚገልጹት አቶ እውነቱ ብዝሃነት በአብሮነት ሂደት ሊጎለብት የሚገባ የመስተጋብር ውጤት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በሌላም በኩል ብዝሃነት ከመቻቻል ባለፈ ልዩነቶቻችን በፈጠሯቸው እሴቶች እና ለልዩነታችን መኖር ምክንያት በሆኑ ማንነቶቻችን ላይ መግባባት እና የጋራ ግንዛቤ መፍጠር ማለትም መሆኑን ይገልጻሉ አቶ እውነቱ፡፡

በአጠቃላይ ብዝሃነትን የውይይት፣ ድርድር እንዲሁም የሰጥቶ መቀበል ባህል መጎልበት ውጤት ሆኖ እናገኘዋለን የሚሉት አቶ እውነቱ ለስኬቱ ከመነሻው እስከ መድረሻው ለጉዳዩ ተግባቦት ቅን እና ፅኑ ፍላጐትን የሚጠይቅ፤ መልካምና ገንቢ የመወያያ ሃሳቦችንም ማስተናገድ የሚጠይቅ ነው ይላሉ፡፡

ብዝሃነት እንዲጎለብት በአንድ በኩል ልዩነታችንን አክብሮ በአንድነት ለመኖር የሚጠቅሙን አስተሳሰ ቦችንና ግንኙነቶችን ማዳበር የሚያስፈልግ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ አንዱ ከሌላው ጋር የሚጋራቸው መደበኛ ያልሆኑ መግባቢያዎች ጭምር ብዝሃነትን የሚያከብሩና የሚያንፀባርቁ መሆን ይገባቸዋል ይላሉ አቶ እውነቱ ጽሁፋቸውን ሲያጠቃልሉ፡፡

ብዝሃነትና ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ወይም ዘመናት ብዝሃነትን መቀበልና ማክበር ይቅርና በተፈጥሮ ብቻ በውስጧ ያለውን ልዩነት እንኳን ማስተናገድ ተስኗት መቆየቷን የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ህብረ-ብሔራዊት የሆነችው ሀገራችን በውስጧ ያሉትን ልዩነቶች ማስተናገድ ባለመቻሏ በእርስ በእርስ ጦርነት ስትናጥና የኋልዮሽ ስትጓዝ ቆይታለች ፡፡

አገሪቱ  ህብረ-ብሔራዊነትን ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀበለችው በሽግግሩ ዘመን ቻርተር ኋላም በ1987 በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት መረጃ ያመላከታል፡፡

ኢትዮጵያ ልዩነቶችን አምና ለመቀበል ረጅም ዘመናትና መራራ ትግል ቢጠይቃትም አሁን ከዚያ ሁሉ አስከፊ ጊዜ አልፋ ብዝሃነትን በተግባር ለማረጋገጥ ረጅሙን ጉዞ ከጀመረች ሰንበትበት ብላለች፡፡

የብዝሃነት መረጋገጥ እንደ እኛ ባለ ህብረ ብሔራዊ ሀገር የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ማስፈኛ ወሳኝ መሠረት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

በሀገራችን ብዝሃነትን እውን ለማድረግ ከሚሠሩ ሥራዎች የመጀመሪያዎቹ በህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ ላይ በቂ ግንዛቤ፣ መግባባት እና የአመለካከት የበላይነት በሁሉም ደረጃ ማረጋገጥ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር መሆኑን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ለብዝሃነት መሠረት በሆነው የፌዴራል ሥርዓቱ ላይ በቂ ግንዛቤ ሳይኖር የሚሰራ ሥራ ለአንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ግንባታ፣ በተለይም ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ልማት በጎ አስተዋፅኦ እንደማይኖረው ይታመናል፡፡ በመሆኑም ስለብዝሃነት መሠረታዊ መነሻና መድረሻ በአግባቡ መረዳት ያሻል::

በመጨረሻም የዘርፉ ጠቢባን ብዝሃነት ከባድና አድካሚ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሂደት ውስጥ ታልፎ የሚገኝ ወይም የሚደረስ መሆኑን ለማስረዳት ሲሉ ህብረ ብሔራዊነትን እንደ ድፍድፍ ነዳጅ ይመስሉታል፤ ብዝሃነትን ደግሞ እንደ ተጣራ ነዳጅ እና እንደነጠረ ወርቅ ወይም ውድ ማዕድን ይቆጥሩታል፡፡

ለዚህም ብዝሃነትን በማክበርና በማስተናገድ ከዚህ የሚገኘውን ወርቅና የተጣራ ነዳጅ ለመቋደስ በሚመለካታቸው አካላት ዕውቀትን መሰረት ያደረጉ ስራዎች መስራት ይኖርባቸዋል፡፡