*41 ባቡሮች

የአዲስ አበባ ቀላል በባቡር ፕሮጀክት በ41 ባቡሮች አገልግሎት ይሰጣል፡፡ 21ዱ ባቡሮች ለምስራቅ-ምዕራብ አገልግሎት የሚውሉ ሲሆን 20ዎቹ ደግሞ በሰሜን-ደቡብ መስመር አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡

የቀላል ባቡሩ ተሸከርካሪዎች በቻይናው ቻንግቹን ሬይልዌይ ቬህክልስ /CHANGCHUN RAILWAY VEHICLES/ ዲዛይን ተደርገው የተመረቱ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ተሸከርካሪዎች ቀለም በህብረተሰቡ በተመረጠው መሰረት የተመረቱ ናቸው፡፡         

አንዱ የቀላል ባቡር ተሸከርካሪ 44 ቶን ይመዝናል፣ ርዝመቱ 29 ነጥብ 5 ሜትር ሲሆን ስፋቱ ደግሞ 2 ነጥብ 6 ሜትር ነው፡፡

ባቡሩ የዲዛይን ፍጥነቱ 80 ኪ.ሜ በሰአት ሲሆን የኦፕሬሽን ፍጥነቱ 70 ኪ.ሜ በሰአት ነው፡፡

አዲስ አበባ ከዋና ከተማነት አልፋ የአፍሪካም ዋና ከተማ በመሆኗ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ግንባታ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት ከመሆንም አልፎ አገራችን የደረሰችበትን የእድገት እና ስልጣኔ ደረጃ ለማንፀባረቅ ታሳቢ ተደርጎ ዲዛይን ተደርጓል፡፡

በተጨማሪም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የተሸከርካሪ፣ የመሳፈሪያ ጣቢያ እና በቀላል ባቡር ላይ ያሉት የእጅ መደገፊያዎች ከአገራችን የሰንደቃላማ ቀለሞች ላይ ተመርጠው እንዲወሰዱ ተደርጓል ፡፡

 

*ተመጣጣኝ ክፍያ

የባቡሩ የመነሻ ዋጋ 2 ብር ሲሆን እስከ 4 ኪሎ ሜትሮች አልያም 8 የማቆሚያ ጣቢያዎች ድረስ ያስጠቅማል፡፡

ከ4 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር እስከ 8 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ወይንም 14 የባቡር ማቆሚያ ጣቢያዎች ድረስ ያለው ዋጋ ደግሞ 4 ብር ሆኗል፡፡

የባቡር ታሪፉ ከፍተኛ ክፍያ 6 ብር ሲሆን ከመነሻው አንስቶ እስከ መድረሻው ድረስ ያለውን 17 ኪሎ ሜትሮች ለመጓዝ ያስችላል፡፡

የባቡሩ ዋጋ የታክሲ፣ የሃይገርና የአንበሳ አውቶብስ የክፍያ ዋጋዎችን በማጥናትና የህብረተሰቡን ገቢ በማገናዘብ የተከናወነ ነው።

የክፍያ ስርዓቱ በወረቀትና በኤሌክትሮኒክስ ካርዶች አማካኝነት የሚፈፀም ሲሆን ሳይከፍሉ የሚጓጓዙ መንገደኞችን በስውር በሚገጠሙ ካሜራዎች በመለየት የተጓዙበትን መንገድ ዋጋ በ10 በማባዛት እንዲከፍሉ ይደረጋል።

 

*አካል ጉዳተኞች

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት በድልድይ፣ በመሬት ውስጥ እና በከፊል የመሬት ውስጥ ፌርማታዎች ላይ ለአቅመ ደካሞችና ለአካል ጉዳተኞች ዘመናዊ መወጣጫዎች (Escalator) እና አሳንሰሮች (Elevator) አሉት፡፡

በባቡር መስመሩ ላይ በአጠቃላይ 22 አሳንሰሮች (Elevator) እና የ12 መወጣጫዎች (Escalator) አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡

 

*39 የመሳፈሪያ ጣቢያዎች

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በሁሉም የግንባታው መስመሮች ላይ በአጠቃላይ 39 የመሳፈሪያ ጣቢያዎች ሲኖሩት ከነዚህም መካከል 9 የድልድይ፣ 27 የመሬት ላይ፣ 1 የመሬት ውስጥ እና 2 ከፊል የመሬት ውስጥ ፌርማታዎች ናቸው፡፡

የድልድይ፣ የመሬት ላይ እና የከፊል የመሬት ውስጥ መሳፈሪያ ጣቢያዎቹ የዝናብ መከላከያዎች ዲዛይን የአረንጓዴ ልማት መርህን የተከተለ ነው፡፡  

የምስራቅ-ምዕራብ መስመር በምዕራብ በኩል ከጦር ሀይሎች ተነስቶ በልደታ ቤተክርስቲያን፣ ሜክሲኮ አደባባይ፣ መስቀል አደባባይ፣ ኡራኤል አደባባይ፣ ሀያ ሁለት፣ መገናኛ አደባባይ፣ ሲ ኤ ምሲን አቋርጦ አያት አደባባይ ከመድረሱ በፊት ያለውን የከተማው ክፍል የሚያጠቃልል ነው፡፡

የምስራቅ-ምዕራብ መስመር የግንባታ ክፍል ላይ 13 ነጥብ 92 ኪሜ የመሬት ላይ ግንባታና 3 ነጥብ 92 ኪሜ የድልድይ ላይ ግንባታ የጋራ መስመሩን ጨምሮ የሚያጠቃልል ሲሆን በዚሁ የግንባታ ክፍል ላይ 22 የመሳፈሪያ ጣቢያዎች አሉ፡፡

ጣቢያዎቹ 14 የመሬት ላይ፣ 6 የድልድይ ላይ እና 2 ከፊል የመሬት ውስጥ የመሳፈሪያ ጣቢያ ናቸው፡፡

ከፍተኛው የመሳፈሪያ ጣቢያ ርቀት 1260 ሜትር ሲሆን ዝቅተኛው ደግሞ 445 ሜትር ነው፡፡ በአማካይ የመሳፈሪያ ጣቢያዎች ርቀት 794 ሜትር ነው፡፡

የሰሜን-ደቡብ መስመር በሰሜን በኩል ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክርስቲያን ተነስቶ በመርካቶ፣ አውቶብስ ተራ፣ ሰባተኛ፣ አብነት፣ ልደታ፣ መስቀል አደባባይ አድርጎ መሿለኪያ አደባባይ፣ ጎተራ፣ ሳሪስን አቋርጦ ቃሊት ላይ የሚያልቅ ነው፡፡

የሰሜን-ደቡብ መስመር 10 ንጥብ 06 ኪሜ የመሬት ክፍል፣ 5 ነጥብ 907 ኪሜ የድልድይ ላይ ግንባታ የጋራ መስመሩን ጨምሮ እንዲሁም 0 ነጥብ 668 ሜትር የመሬት ውስጥ ክፍል የሚያካትት ነው፡፡

በሰሜን-ደቡብ መስመር በአጠቃላይ 22 የመሳፈሪያ ጣቢያዎች ሲኖሩ 8 የድልድይ ላይ የመሳፈሪያ ጣቢያ ማለትም የጋራ መስመሩን ጨምሮ፣ 13 የመሬት ላይ ፌርማታ እና 1 የመሬት ውስጥ ፌርማታ ናቸው፡፡

ከፍተኛው የመሳፈሪያ ጣቢያ ርቀት 1969 ሜትር ሲሆን ዝቅተኛው ደግሞ 445 ሜትር ነው፡፡ በአማካኝ የመሳፈሪያ ጣቢያዎች ርቀት 772 ሜትር ነው፡፡

በሁሉም የግንባታው መስመሮች ላይ በአጠቃላይ 39 የመሳፈሪያ ጣቢያዎች ሲኖሩ ከነዚህም መካከል 9 የድልድይ ላይ፣ 27 የመሬት ላይ፣ 1 የመሬት ውስጥ እና 2 ከፊል የመሬት ውስጥ ፌርማታዎች ይገኙበታል፡፡

የመሳፈሪያ ጣቢያዎች ዲዛይን የተደረጉት አብዛኛውን የተሳፋሪ እንቅስቃሴ የተመቻቸ እንዲሆን እና የኦፕሬሽን አገልግሎቱን የተቀላጠፈ እንዲሆን ለማድረግ የታስቦ ነው፡፡

ሁሉም የመሳፈሪያ ጣበያዎች መውጫና መግቢያ አካባቢውን መሰረት ያደረገ እና ደህንነቱን የጠበቀ እንዲሁም የከተማዋን መሬት አቀማመጥ መሰረት አድርጎ ተገንብቷል፡፡

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት የመጀመሪያው ምዕራፍ በምስራቅ-ምዕራብ እና በሰሜን-ደቡብ መስመር 31 ነጥብ 048 ኪ.ሜ ሲሆን ሁለቱ መስመሮች የሚጋሩትን 2 ነጥብ 662 ኪ.ሜ ጨምሮ የከተማዋን ዋና መስመር የሚሸፍን ነው፡፡

 

*ቃሊቲ ዲፖል

የቀላል ባቡር የቁጥጥር ማዕከሉ OCC (Operation Control Center) በቃሊቲ ዲፖ ውስጥ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት የቃሊቲ ዲፖና የአያት ዲፖ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ዋና የባቡር ዲፖዎች አሉት፡፡ 

የቃሊቲ ዲፖ 107 ሺ ስኩዊር ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን በውስጡም የተለያዩ ለቢሮ አግልግሎት የሚውሉ ህንፃዎች፣ የባቡሮች ማደርያ እና መጠገኛ ወርክ ሾፖች፣ የውሃ እና ፍሳሽ ማጣሪያ፤ የሃይል መስጫ ጣቢያ እና የቀላል ባቡር አገልግሎት የመቆጣጠርያ ዋነኛው ክፍልም እዚህ ይገኛል፡፡         

የቃሊቲ ዲፖ የሰሜን-ደቡቡን እና የምስራቅ- ምዕራብ ባቡሮችን የመቆጣጠር፤ የባቡሮችን የማሰማራት፤ የጥገና እና የባቡር ምርመራ ስራ የሚከናወንበት ነው፡፡

የአያት ዲፖ በ72 ሺ ስኩዊር ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን ሲሆን በውስጡም የተለያዩ ለቢሮ አግልግሎት የሚውሉ ህንፃዎች፣ የባቡሮች ማደርያ እና መጠገኛ ወርክ ሾፖች፣ የውሃ እና ፍሳሽ ማጣሪያ፤ የሃይል መስጫ ጣቢያ የሲግናሊንግ ቤቶች እና የመሳሰሉት በዲፖው ወስጥ ይገኛል፡፡

የአያት ዲፖ የምስራቅ-ምዕራቡን የጥገና የቴክኒካል ምርመራ እና የምስራቅ-ምዕራብ ባቡሮች ማደርያ በመሆን ያገለግላል፡፡       

 

*አስተማማኝ የሃይል አቅርቦት

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በአጠቃላይ 20 የሃይል መስጫ ጣቢያዎች አሉት፡፡ ከጣቢያዎቹ 18ቱ በዋናው መስመር ላይ ሲገኙ የቀሩት ሁለት ጣቢያዎች በቃሊቲ ዲፖ እና በአያት ዲፖ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

የሃይል አቅርቦቱ የloop-in & loop-out power system ሲሆን የ15 kva ሃይል በሁሉም የቀላል ባቡር የሃይል መቀበያ ጣቢያዎች ላይ ተገጥሟል፡፡

በቀላል ባቡር የሚገኙ የኃይል አቅርቦት ጣቢያዎችንና ሙሉ የDC ኤሌክትሪክ መስመሮችን መረጃ የሚሰበስብና የሚቆጣጠር ሲስተም በአገልግሎት መቆጣጠርያ ክፍል (OCC) የተገጠመ ስለሆነ ማንኛውንም አይነት የእክል አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ በመስጠት በጊዜ የመቆጣጠርና ለደህንነት አስተማማኝነት በመስራት የኃይል አቅርቦትን አገልግሎትና ጥገናን ለማከናወን ይረዳል፡፡      

ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት የባቡር ኤሌክትሪክ ኃይል መሰብሰቢያ መስመሮች ሲስተም DC 750V ሲሆን ይህንን መስመር የሚሸከሙት H type የብረት ምሰሶዎች በድልድይና በመሬት ላይ መስመሮች የተተገበረ ሲሆን በዋሻ ውስጥ በግድግዳ ላይ የሚገጠም ማንጠልጠያ ይጠቀማሉ፡፡   

የኮሚዩኒኬሽን  ሲስተሙ በአሁኑ  ሰዓት  በአስተማማኝ  ሁኔታ  በመስራት  ላይ  ሲገኝ  ለባቡር  አገልግሎቱም  የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት  ለመስጠት  ተዘጋጅቷል፡፡

 

*የካሜራ ቁጥጥር

የደህንነት ካሜራዎች (CCTV) የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ስርዓት ዘመናዊነት አንዱ አካል ነው፡፡

በዚህ ሲስተም ከማዕከላዊ የመቆጣጠሪያ ጣቢያ በመሆን የተሳፋሪዎችን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለመከታተል ያስችላል፡፡

በመንገዶች ማቋረጫ ያለው የትራፊክ እንቅስቃሴም ከካሜራዎቹ እይታ ውጭ አይደሉም፡፡

የደህንነት ካሜራዎቹ መኖር በአጠቃላይ የመቆጣጠር ስራዎችን በመስራት የአገልግሎቱን አስተዳደር ቅልጥፍናና ብቃት በማሻሻል ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ይረዳል፡፡

በናትናኤል ፀጋዬ