በ500 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እየተከናወነ ያለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ አብዮት

በዳንኤል ንጉሴ

የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊዎእ ቁጥራቸው ከ16 ወደ 24 ማደጉ ተከተሎ የአህጉሩን ውድድር የማዘጋጀት አቅም ያላቸው ሀገራት ቁጥር ጥቂት ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያም ይህንን የአህጉሩን ታላቅ የእግር ኳስ ውድድር ለማዘጋጀት ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ በመመደብ ውድድሩን ከሚያዘጋጁ ጥቂት ሀገራት ለመሰለፍ አዳዲስ የሰታዲየም ግንባታዎችን በመላው ሀገር እያከናወነች ትግኛለች፡፡

ሀገሪቱ በያዘችው ሁለተኛው የእድገት አና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ከ13 በላይ አዳዲስ እስታዲየሞችን በግንባታ ላይ ናቸው፡፡

የአፍሪካን እግር ኳስ ውድድሮችን በማዘጋጀት ረገድ ወደ ኋላ ቀርታ የነበረችው ኢትዮጵያ የአህጉሩን ታላቅ የእግር ኳስ ውድድርን እአአ በ2020 ለማዘጋጀት ለካፍ እቅዷን አስገብታለች፡፡

ይህም ገና በይፋ የታወጀ ባይሆንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጁነዲን ባሻ   ውድድሩን የማዘጋጀት መብታቸውን እንደሚያስጠብቁ ተናግረዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2020 የሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበትን የቻን ውድድር ለማስተናገድ ጥያቄ ያቀረበችው ኢትዮጵያ ጥያቄው ከተሳካ እአአ በ2025 የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ጥሩ መሰረት እንደሚሆንላት እየተነገረ ነው፡፡

የካፍን ውሳኔ ለማግኘት ግን የስታዲየሞቹ ግንባታ ተጠናቀው ለውድድሩ ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ጂነዲን ባሻ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግንባታቸው እየተካሄዱ ካሉ ስታዲዬሞች መካከል 60 ሺህ መቀመጫ ያለው የአዲስ አበባ ብሄራዊ ስታዲየም 110 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እየተገነባ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ 45 መቀመጫዎች ያሉት የመቀሌ ስታዲየም በ20 ሚሊዮን ዶላር፤ 80 ሺህ መቀመጫዎች ያሉት የአዳማ ስታዲየም በ80 ሚሊዮን ዶላር፤ 70 ሺህ መቀመጫዎች ያሉት የድሬዳዋ ስታዲየም በ50 ሚሊዮን ዶላር፣ 56 ሺህ መቀመጫዎች ያሉት የሃረር ስታዲየም በ70 ሚሊዮን ዶላር ፤30 ሺህ መቀመጫዎች ያለው የጋምቤላ ስታዲየም በ20 ሚሊየን ዶላር በመገንባት ላይ ናቸው፡፡

ጥቂቶቹ የተጠናቀቁ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ በ25 ሚሊዮን የተገነባው 25,155 መቀመጫዎች ያሉት የወልዲያ ስታዲየም፤ በ25 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው 40,000 መቀመጫ ያለው የሀዋሳ ስቴድየም   እና ከ25 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገበት 53 ሺህ መቀመጫዎች ያሉት የባህር ዳር ስቴዲየም ይገኙበታል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ የተገኙት የካፍ ፕሬዝዳንት አህመድ አህመድ ከጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ጋር በተወያዩበት ወቅት በመሠረተ-ልማት ላይ በሚካሄዱ ማሻሻያዎች የተደሰቱ መሆናቸውን ገልጸዋል.

ይህ ታላቅ ህዝብ እና በአሁኑ ጊዜ የምናየው ተግባር ኢትዮጵያ ለወደፊቱ ዝግጁ መሆኗን ያመለክታል በማለት ለካፍ ድህረገጸ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከካፍ አራት መስራች አባላት መካከል አንዷ የነበረች ሲሆን በ1962 ዋንጫውን ካነሳች በኃላ 30 ዓመታት ወደ መድረኩ ሳትሳተፍ ቆይታ በ2005 ዓ.ም የአፍሪካ ዋንጫ በደቡብ አፍሪካ ውድድር ለመሳተፍ ችላለች፡፡

አዲስ አበባ እና ሌሎች የክልል ዋና ከተሞች እንደ ባህር ዳር, ሀዋሳ, መቀሌ እና ድሬዳዋ ያሉት በቂ የሆነ የሆቴልና መዝናኛ መስተንዶ ስላላቸው በመጪዎች አመታት በርካታ ስራዎችን በማከናወን  አህጉራዊ ውድድሮችን ለማዘጋጀት መታቀዱን አቶ ጁነዲን ባሻ ገልጸዋል፡፡