የአቦ ሸማኔ ዝርያ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል

ታህሳስ 18 ፣2009

በአለማችን ፈጣኑ የዱር እንስሳ የሆነው አቦ ሸማኔ ቁጥሩ እየተመናመነ በመምጣቱ ዝርያው ሊጠፋ መሆኑነን አንድ ጥናት አመለከተ፡፡

እንደ ጥናቱ ግኝት የዱር እንስሳው ዝርያ እዚህ አደጋ ላይ የወደቀው በቂ ጥበቃ ከሚደረግለት አካባቢ ስለራቀና ከሰዎች ጋር ያለው ግጭት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ነው የተባለው፡፡

በአለማችን 7 ሺህ 100 ገደማ ፈጣን የዱር እንስሳት ብቻ እንዳሉም ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ ውስጥ በምድራችን በህይወት ከሚገኙ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የአቦሸማኔ ዝርያዎች የሚኖሩት በደቡባዊ አፍሪካ ክልል በስድስት ሀገሮች ላይ እንደሆነ ጥናቱ ጠቅሷል፡፡

ይሁንና የእንስሳው ዝርያ በኢሲያ ክፉኛ ስለተመናመነ ጠፍቷል በሚያስብል ደረጃ ላይ እንደደረሰ ተነግሯል፡፡

አቦ ሸማኔ በባህሪው በአንድ አካባቢ ላይ የሚሰፍር ሳይሆን ጥበቃ በሚያገኝበት በተለያዩ የዱር ስፍራዎች የሚኖር በመሆኑ ለመጥፋት አደጋ ተጋላጭ አድርጎታልም ተብሏል፡፡

በዚህም 77 በመቶ የሚሆነው የእንስሳው ዝርያው የሚኖረው በአንፃሩ የደህንነት ጥበቃ ከሚያገኙበት ፓርኮችና ማቆያዎች ውጪ እርቆ ነው ብሏል ጥናቱ፡፡ 

ከዚህ ባለፈ ደግሞ እንስሳው የሰፈረበት መሬት በአርሶ አደሮች እየለማ መምጣቱን ተከትሎ ዝርያው በህይወት ለመቆየት አዳጋች ሆኖበታል ነው የተባለው፡፡

ከመሬት ይዞታ ለውጥ ጋር ተያይዞም በዝምባብዌ ባለፉት 16 ዓመት የአቦሸማኔ ዝርያ በቁጥር ከ1 ሺህ 200 ወደ 170 ወርዶ  እንደተመናመነ ተገልጿል፡፡

በመሆኑም ዝርያዊ አሁን ካለበት ተጋላጭ ከሚለው ምድብ ወጥቶ አስፈላጊው  ጥበቃ  እንዲደረግለት ለመጥፋት የተቃረበ ዝርያ በሚለው  ምድብ እንዲከተት አጥኚዎቹ ገልፀዋል፡፡

አቦሸማኔ በባህሪው እራሱን አግሎ ሚስጢራዊ የአኗኗር ዘይቤ ስለሚከተል በዝርያው ላይ ጠንካራ መረጃ መሰብሰብ አዳጋች ሆኗል ሲሉም በእንግሊዝ ተቀማጭነቱን ባደረገው የዞሎጂካል ሶሳይቲ ኦፍ ለንደን የሚሰሩት ዶ/ር ሳራህ ዱራንት ተናግረዋል፡፡   

ምንጭ፦ቢቢሲ