በመናኸሪያዎች ለተጓዦች ሙሉ የጉዞ መረጃ ማቅረብ የሚያስችል አሰራር ሊዘረጋ ነው

ታህሳስ 30፣2009

በሁሉም የአገሪቱ መናኸሪያዎች ለተጓዦች ሙሉ የጉዞ መረጃ ማቅረብ የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት ሊዘረጋ ነው።

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን እንዳስታወቀው በቴክኖሎጂ የሚታገዘው ይኸው አሰራር የመንገደኞችን ጊዜና ወጪ የሚቆጥብ ነው።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ኃይለማርያም እንደገለጹት ነባሩ አሰራር አድካሚና ለወጪ የሚዳርግ ከመሆኑ ባሻገር ተጓዦችን ለአዳጋ የሚያጋልጥበት ሁኔታ ተስተውሏል።

''አሁን ባለው አሰራር መንገደኞች በብዙ እንግልት ትኬት ከገዙ በኋላ ጧት መኪናውን ፈልጎ ለማግኘት ጊዜና ጉልበታቸውን ከማባከን ባለፈ ለስርቆት ይጋለጣሉ፤ እናም ይህን የሚያስቀር አሰራር ነው ተግባራዊ የሚሆነው'' ብለዋል።

በዚህም ተገልጋዮች የትኬት ቦታ፣ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ቁጥርና መቆሚያ እንዲሁም የመነሻና መድረሻ ሰዓታቸውን ጭምር በቀላሉ ለይተው ማወቅ እንደሚችሉ ነው የተናገሩት።

መረጃው ተሽከርካሪዎች ከመናኸሪያ ከመውጣታቸው በፊት የቆሙበትን ቦታ በግልጽ የሚያመላክት እንደሆነም አስረድተዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ከክልል የትራንስፖርት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር የተደረገ ሲሆን በዚህ ዓመትም ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

አሁን አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉት መናኸሪያዎችና ተሽከርካሪዎች አሰራሩን በቴክኖሎጅ የታገዘ ለማድረግ ብዙም አመቺ እንዳልሆኑ ይገለጹት ዳይሬክተሩ

ነባር መናኸሪያዎችን የማደስና አዳዲስ የሚገነቡት ደግም ለቴክኖሎጂው ምቹ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ ቀደሚ ይሆናል ብለዋል ።

አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችም መስፈርት ወጥቶላቸው ባለኃብቶችም በመስፈርቱ መሰረት ከሚዘረጋው አገልግሎት ጋር የተጣጣመ ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው ተሽከርካሪዎች እንዲያቀርቡ ይደረጋል ማልታችውን ኢዜአ ዘግቧል።