የባአካር የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ መሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ

የካቲት 14፣ 2009

የባአካር የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ መሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ቦታው በመገኘት የመሰረተ ድንጋዩን አስቀምጠዋል፡፡

የመጀመሪያው ምዕራፍ የፓርኩ ግንባታ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚጠይቅ ሲሆን በሁለት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡

አጠቃላይ ስራው በአራት ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቀው ፓርክ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ለባለሃብቶች ክፍት ይሆናል፡፡

በመሰረተ ድንጋይ ማስቀመጥ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት ፓርኩ በአካባቢው የሚመረተው ሰሊጥ እሴት እንዲጨመርበት ያግዛል፡፡

በዚህም ፓርኩ የአርሶ አደሮችን ህይወት ለመለወጥ ዓላማው አድርጎ ይገነባል ብለዋል፡፡

ፓርኩ ከወልቃይት ስኳር ፋብሪካ እና ከተከዜ ወንዝ ግድብ ጋር ተሳስሮ የሚገነባ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በትግራይ ክልል ከሚገነባው ባአካር የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ በተጨማሪ ሶስት ሌሎች ፓርኮች በደቡብ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች ይገነባሉ፡፡

የአራቱም ፓርኮች ግንባታ በአራት ዓመት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል፡፡

ከአራቱ ፓርኮች ግንባታ በኋላ ደግሞ ተጨማሪ 13 የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ይገነባሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ተአምርአየሁ ወንድማገኝ