ትራምፕ ለኮንግረሱ ተስፋ ሰጪ ንግግር አደረጉ

የካቲት 22፣ 2009

45ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያ የኮንግረስ ንግግራቸው ተስፋ ሰጪ እና መተማመን ያለበት ንግግር ማድረጋቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው፡፡

ንግግሩ ፕሬዝዳንታዊ ሹመታቸውን ሲቀበሉ ካደረጉት የተሻለ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ትራምፕ በንግግራቸው ያረርጀውን የአሜሪካ መሰረተ ልማት ለመጠገን የአንድ ትሪሊዮን ዶላር በጀት እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

ይህ በጀትም አሜሪካን ከማደስ በተጓዳኝ ለሚሊዮኖች የስራ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

የወቅቱ የአሜሪካ የስደተኞች ህግ አሜሪካን በቢሊዮን ዶላር እያስከፈላት መሆኑን ያወሱት ትራምፕ የሀገሪቱን ፀጥታ ለመጠበቅ እና የአሜሪካን ህዝብ ጥቅም ለማስከበር ሲባል የስደተኞችን ህግ ማሻሻል አለብን ብለዋል፡፡

በፕሬዝዳንታዊ ምርጫዬ ቃል እንደገባሁት በሀገሪቱ ወንጀለኛ ስደተኞችን ወደ መጡበት መመለስ እና በሜክሲኮ ድንበር ታላቁን ግንብ የመገንባት እቅዳችን ይተገበራል ሲሉም ትራምፕ አረጋግጠዋል፡፡

አሜሪካ ፅንፈኞችን ከወዳጆቿ ጋር ሆና መዋጋቷን ትቀጥላለች ያሉት ትራምፕ አይ ኤስ አይ ኤስን የማጥፋት ዘመቻው በሰፊው እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡

የአሜሪካን መከላከያ ለማዘመንም ትራምፕ ከተለመደው ከፍተኛ በጀት ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኦባማ ኬር የጤና መድህን ደሃውን የአሜሪካ ህዝብ ተጠቃሚ ባለማድረጉ መቀየር አለበት ያሉት ትራምፕ እንደግዛቶች ተጨባጭ ሁኔታ የሚተገበር እና መድሃኒቶችን በረከሰ ዋጋ የሚያቀርብ የጤና መድህን ይቀርባል ሲሉ ዕቅዳቸውን አስቀምጠዋል፡፡

የአሜሪካ ኩባንያዎችን የሚያበረታታ ስርዓት በመዘርጋት ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠር ሌላው መርሃቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአሜሪካ ምርቶች ላይ የገዘፈ ቀረጥ የሚጥሉ ሀገራት ወደ አሜሪካ ምርቶቻቸውን በነጻ እንዲያሰገቡ መፈቀድ የለበትም ያሉት ትራምፕ  በነፃ ንግድ አምናለሁ ነገር ግን ፍትሃዊ ሊሆን ይግባል ብለዋል ፡፡

ትራምፕ በመጨረሻም ሁለቱ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች እቅዱን ለማስፈፀም በጋራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡

የዘገባው ምንጭ፡- ብሉምበርግ፣ ቢቢሲ፣ ሲኤን ኤን