በአይሲቲ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶችን አቅም ለማሳደግ ስትራቴጂክ ፕላን እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ

የካቲት 24፣ 2009

በኢትዮጵያ በአይሲቲ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶችን አቅም ለማሳደግ ስትራቴጂክ ፕላን እየተዘጋጀ መሆኑን የመገናኛና ኢንፎርሽን ቴክኖሎጂ ሚንስትር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡

ፕላኑ ድርጅቶች በአይሲቲ ዘርፍ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ እንዲገቡ ይረዳቸዋል ተብሏል፡፡

አይ ሲቲ መንደር በ480 ሚሊዮን ብር የሶፍት ዌር ማበልጸጊያ ማዕከል ለመገንባት የመሰረተ ድንጋይ ተቀምጧል፡፡

ማዕከሉን የሚያስገነባው አገር በቀል ተቋም የሲኔት ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ነው።

የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ለማዕከሉ መገንባት የመሰረት ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ አገሮች ያሉባቸውን የእድገት ክፈተቶች ለመሙላት ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትልቅ ሞተር ነው።

እንደ ኢትዮጵያ በዕድገት ሂደት ላይ ለሚገኙ አገሮች የቴክኖሎጂ መስፋፋት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ባለፈው ዓመት የተመረቀው የኢትዮ አይ ሲቲ መንደር በአሁኑ ወቅት ወደ 20 የሚሆኑ የአገር በቀል ተቋማት ገብቶ እየሰሩበት ይገኛል።

በቀጣይም "ለአገር በቀል ተቋማት ልምድ ማካፈል የሚችሉ የውጭ ተቋማት እንዲገቡ ይደረጋል" ብለዋል።

የሶፍት ዌር ማበልጸጊያ ማዕከሉ ግንባታ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገልግሎት በመስጠት የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ትልቅ ስራ እያከናወነ መሆኑን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

የሲኔት ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ ፈጥኖ ወደ ስራ በመግባት ከአገር ውስጥ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆኑን ጠቁመው፤ ለአገሪቷ የውጭ ምንዛሪ በሚያስገኝ ደረጃ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በአይ ሲቲ መንደሩ ያሉ ተቋማት የዓለም አቀፍ ደረጃ መስፈርት አሟልተው ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው ያመለከቱት ዶክተር ደብረጽዮን፤ "መንግስት የተለያዩ ሥልጠናዎችና ልምዶች የሚያገኙበት መንገድ ያመቻቻል" ብለዋል።

የሲኔት ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በእምነት ደምሴ በበኩላቸው  የሚገነባው ማዕከል የሶፍትዌር ማልሚያ፣ ማበልጸጊያ፣ ክላውድ ኮምፒውቲንግና ምርመራ ማካሄጃ ይሆናል።

"የማዕከሉ መገንባት የአገሪቷን ቴክኖሎጂ በማሳደግና ለውጭ ምንዛሪ መገኘት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል" ብለዋል።

ማዕከሉ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ከ1 ሺ 100 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች የስራ ዕድል እንደሚፈጠር ታውቋል።

ሪፖርተር፡- ፋሲካ አያሌው