የአፍሪካን ህዳሴ ለማረጋገጥ በጽናትና በአንድነት መታገልን ከአድዋ ድል መማር ይገባል - ታቦ ኢምቤኪ

የካቲት 26፣ 2009

አፍሪካውያን የሚያጋጥማቸውን ፈተናዎች አልፈው ወደ ብልጽግና ለመሸጋገር በጽናትና በአንድነት መታገልን ከአድዋ ድል መማር እንደሚገባቸው የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ታቦ ኢምቤኪ ገለጹ።

121ኛውን የአድዋ ድል በዓልን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ከአድዋ ድል ጋር በተያያዘ ድሉ ለአፍሪካ ነጻነት የነበረው ሚና፣ አፍሪካውያን ከድሉ ምን ሊማሩ ይችላሉ? የአፍሪካን ህዳሴ እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል? የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን ለታቦ ኢምቤኪ ሰንዝረዋል።

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኢምቤኪ በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያውያን ቅኝ ግዛት ለማስፋፋት ባህር አቋርጦ በመጣው የጣልያን ጦር ላይ የተቀዳጁት ድል የራሳቸው ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያንም ጭምር መሆኑን ነው አጽንኦት የሰጡት።

''ድሉ በቅኝ ግዛትና ኢምፔሪያሊዝም ቀምበር ስር ለነበሩ የአፍሪካ አገሮች የማንቂያ ደውል ነበር'' ያሉት የቀድሞው ፕሬዚዳንት፤ ድሉ የአፍሪካውያንን በራስ የመተማመን መንፈስ የገነባ እንደነበር አስታውሰዋል።  

''ለዚህም ነው አፍሪካና ኢትዮጵያ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ተደርገው የሚወሰዱት" ብለዋል።  

አፍሪካ በአዝጋሚ የለውጥ ሂደት ውስጥ መሆኗን የተገሩት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኢምቤኪ፤ "የአህጉሪቷን ህዳሴ በማረጋገጥና የሚጠበቀውን ለውጥ በማምጣት አፍሪካውያን ከአድዋ ታሪካዊ ድል አንድነትን መማር ይገባቸዋል" ብለዋል።

ድህነት አሁንም የአፍሪካውያን ፈተና መሆኑን ገልጸው፤ ሥር የሰደደ ሙስና አህጉሪቷ ለውጥ እንዳታመጣ ተብትበው ከያዙዋት ችግሮች መካከል ተጠቃሽ መሆኑን አውስተዋል። 

"የአድዋ ድል በዚህ በኩል የዓላማ ጽናት የሚያስተምር በመሆኑ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ለጋራ ለውጥ ከድሉ መማር ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል።

ድሉ ለአፍሪካውያን ነጻነት የተጫወተውን ሚናም በሁሉም አፍሪካውያን ዘንድ በአግባቡ ለማስገንዘብ የጋራ ጥረት መደረግ እንዳለበት አመልክተዋል። ድሉን የመዘከር ሂደትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም እንዲሁ።  

''አድዋ፣ ኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ ነጻነትና አንድነት የተሳሰሩ ጉዳዮች ናቸው'' ያሉት ደግሞ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደ ማሪያም ናቸው።

የአድዋ ድል ለጥቁር ህዝቦች ያለውን ትርጉም በስፋት የማስገንዘቡ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል። 

በፓናል ወይይቱ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን፣ተማሪዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።