ናይጄሪያ የፀሀይ ሀይልን ለማልማት እየሰራች ነው

የካቲት 28፣ 2009

በነዳጅ ሀብቷ የበለፀገችው ናይጄሪያ የኤሌክትሪክ ፍጆታዋን ለሟሟላት የፀሀይ ሀይልን ለማልማት ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደሆነ አስታወቀች፡፡

አገሪቱ ከፀሐይ ሀይል 1 ሺህ 200 ሜጋ ዋት ለማመንጨት መወጠኑዋንም የሀገሪቷ ሹማምንት አመልክተዋል፡፡

ይህንንም እውን ለማድረግ የሚረዳ 30 ሚሊዮን ዶላር ለመበጀት የሚረዳ ምክክር በናይጄሪያ ርዕሰ መዲና አቡጃ እየተካሄደ ነው፡፡

አገሪቱ በዘርፉ ፕሮጀክቶች እ.ኤ.አ በ2018 የ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ፍሰት ታስተናግዳለች ሲሉም የናይጄሪያ ታዳሽ ሀይል ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ጎድዊን ኤግቦክሀን ገልፀዋል፡፡

ሀገሪቱ በታዳሽ ሀይል ላይ ለሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ የቦንድ ሽያጭ እንደምታካሄድም ተነግሯል፡፡  

ናይጄሪያ የሚገኙ ቤተሰቦችና አነስተኛ የቢዝነስ ተቋማት የኤሌክትሪክ ሀይል ፍጆታቸውን ለሟሟላት ሲሉ ለጀነሬተሮች በየዓመቱ 21 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ያደርጋሉ፡፡

ይህንን ችግር ለመቀልበስ ከፀሐይ የሚገኝ የኤሌክትሪክ ሀይል አይነተኛና አዋጭ መፍትሄ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ተናግረዋል፡፡

ናይጄሪያ ታዳሽ ሀይል ለአጠቃላይ የኤሌክትሪክ ፍላጎት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ እ.ኤ.አ በ2015 ከነበረው 13 በመቶ ከአስር ዓመት በኋላ 23 በመቶ ለማድረስ ፍላጎት አላት፡፡

ምንጭ፦ብሉምበርግ