የቻይና-አፍሪካ የጋራ ትብብር ይበልጥ እንዲሳለጥ ቻይና ጠየቀች

የካቲት 30፣ 2009

የቻይና አፍሪካ የጋራ ትብብር ይበልጥ እንዲሳለጥ የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ጠየቁ።

ሚኒስትሩ ከ12ኛው የቻይና ሕዝቦች ብሔራዊ ኮንግረስ ዓመታዊ ጉባዔ ጎን ለጎን በሰጡት መግለጫ አገራቸው ከአፍሪካ ጋር ያላት ትብብር እንዲፋጠን ጠይቀዋል።

ቻይና እና አፍሪካ በጥብቅ የተሳሰረ ትብብርና በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ ወንድማማችነት እንዳላቸው ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

"የቻይና አፍሪካ ትብብርን ልዩ የሚያደርገው ነገር ቢኖር ቻይና ሁሌም የገባቸውን ቃል መጠበቋ ነው" ሲሉም አገራቸው የአፍሪካ እውነተኛ አጋር መሆኗን አስረድተዋል።

"ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች አሊያም ኢኮኖሚ የቱንም ያህል ተለዋዋጭ ቢሆኑ ቻይና ለአፍሪካ የምታደርገው ድጋፍ አይቀዛቀዝም" ሲሉም አረጋግጠዋል።

እ.አ.አ በ2015 በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም የአገሪቷ ፕሬዚዳንት ዢ ሺፒንግ ለአፍሪካ 60 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።

ቃል ከተገባው ገንዘብ 60 በመቶ ያህሉ ለአፍሪካ አገራት እንዲደርስ መደረጉን ገልጸው ይህም "ቻይና ቃሏን መጠበቋን የሚያሳይ ነው" ብለዋል።

በዚህም ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የተዘረጋው የባቡር መስመር ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን የሞምባሳ ናይሮቢ የባቡር መስመር በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ነው ሚኒስትሩ ያመለከቱት።

በተጨማሪም በኮንጎ ሪፐብሊክ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን፣ በታንዛኒያ የተቀናጀ የወደብ ልማት እንዲሁም በበርካታ የአፍሪካ አገራት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆኑ በፎረሙ ለአህጉሪቱ የተገባው ቃል መተግበሩን ያሳያል ነው ያሉት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ለአፍሪካ ፍላጎት የተሰጠውን ምላሽ አስመልክተው ሲናገሩ የቻይና አፍሪካ ትብብር ሦስት ሽግግሮችን ማስገኘቱን ይገልፃሉ።

ይህም ከመንግሥታዊ ወደ ገበያ መር፣ ከሸቀጦች ንግድ የንግድ አቅምን ወደ ማጎልበት ትብብር እንዲሁም ከምህንድስና ኮንትራት ወደ ካፒታል ኢንቨስትመንትና ትግበራ መሸጋገሩን ነው የተናገሩት።

በአንፃሩ እነዚህ ሽግግሮች ለአፍሪካ ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ አዲስ አቅምና ዕድሎች ይፈጥሩላታል ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።

"በቻይና-አፍሪካ ትብብር ችግር የለም" የሚሉት ሚኒስትሩ "ሥራዎችና የትብብር ፕሮጀክቶችን ይበልጥ ማሳለጥ ነው የሚያስፈልገው" ሲሉ ተደምጠዋል።

ቻይና የአፍሪካ ሁነኛ የልማት አጋር እንደሆነች ተናግረው ወደፊትም የኢንዱስትሪ ልማትና ግብርናን በማዘመን ብሎም አገር በቀል የልማት አቅምን በማጎልበት አጋርነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

በመጪው ግንቦት ቻይና የ"ዋን ቤልትና ዋን ሮድ ኢኒሼቲቭ ፎረምን ለመጀመሪያ ጊዜ በቤይጂንግ እንደምታስተናግድም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ጠቅሰዋል።

በፎረሙ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርም ደሳለኝን ጨምሮ ከ20 በላይ የአገራት መሪዎች ተካፋይ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

በፎረሙ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር መፍጠር በሚያስችል የፖሊሲ ማዕቀፍ ዙሪያ በመሪዎች ደረጃ ምክክር የሚደረግ ሲሆን ዘላቂ ትብብር ለመፍጠርም መደላድል የመፍጠር ሥራ ይሰራል ነው የተባለው።

ኢኒሼቲቩ የጥንቱን የየብስና የባህር የንግድ መስመር ተከትሎ ቻይናን ከእስያ፣ ከአፍሪካና ከአውሮፓ አገራት ጋር በመሰረተ ልማትና በንግድ ማቆራኘትን ታሳቢ ያደረገ ነው።

ቻይና ኢኒሼቲቩን ገቢራዊ በማድረግ ግልጽ ብሎም የጋራ ትብብርና ተጠቃሚነትን ማስፈን ወደሚያስችል አዲስ ምዕራፍ መሸጋገር እንደምትችል ነው የተነገረው።

ባለፈው ዓመት ቻይና በአፍሪካ ያደረገችው ቀጥተኛ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ከሶስት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ።

ምንጭ፡- ኢዜአ