በአዲስ አበባ የመሠረታዊ ፍጆታ እቃዎች አዲስ የሥርጭት መመሪያ ተዘጋጀ

መጋቢት 4፣ 2009

በአዲስ አበባ የመሠረታዊ ፍጆታ እቃዎች አዲስ የሥርጭት መመሪያ መዘጋጀቱን የከተማው ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡

በአዲስ ተግባራዊ የሚደረገው ይህ አሠራር አሁን የሚስተዋለውን የመሠረታዊ ፍጆታ እቃዎች የሥርጭት መዛባት ለማስተካከል መሆኑን ንግድ ቢሮ ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ሃላፊ አቶ ዲላሞ ኦቶሬ አሠራሩን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ኩፖን መዘጋጀቱን በሠጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

አሠራሩ መንግስት በድጎማ የሚያቀርባቸውን የፓልም ዘይት፣ስኳር እና የስንዴ ዱቄት ብቻ የተመለከተ መሆኑን ነው ያስታወቁት፡፡

ሸማቹ ህብረተሠብም ኩፖኖቹን በወረዳ በኩል የሚያገኝ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ባለው 95ዐሺ የአባወራ እና እማወራ ቁጥር ልክ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡

አሠራሩ በቸርቻሪ ነጋዴውና ሸማቹ መካከል ትስስር በመፍጠር መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች ሥርጭትን በአግባቡ ለመምራት የተዘጋጀ መሆኑንም ነው የገለፁት፡፡

ለዚህም ነጋዴውና ሸማቹ የሚጠቀምባቸው ሁለት አይነት ኩፖኖች የተዘጋጁ ሲሆን በዚህም ሸማቹ ምን ያህል የመሠረታዊ ፍጆታ እቃዎች እንደገዛ እና ነጋዴውም ምን ያህል እንደሸጠ ማወቅ ስለሚቻል የስርጭት መዛባት ችግሩን መከላከል ይችላል ብለዋል፡፡

የኩፖኖቹ ስርጭት ከዚህ ሳምንት ጀምሮ የሚናወን ሲሆን አሠራሩም በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋልም ነው ያሉት፡፡

መንግስት ለሠራተኞች የደሞዝ ማስተካከያ ማድረጉን ተከትሎ የሚታየውን በአንዳንድ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪን ለመከላከል ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲላሞ ኦቶሬ በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡

በጌታቸው ባልቻ