የአፍሪካ መንግስታት ያለባቸውን የሃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት ወጪ ቆጣቢ የሆነ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ እንዲውል ጥሪ ቀረበ

መጋቢት 05፣2009

የአፍሪካ መንግስታት ያለባቸውን የሃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት ወጪ ቆጣቢ የሆነ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ እንዲውል ጥሪ ቀረበ፡፡

የአፍሪካ መንግስታትና ተባባሪዎቻቸው አህጉሪቱ በገጠማት የሃይል አቅርቦት እጥረት ላይያተኮረ መድረክ  በኮትዲቯር ተካሂዷል፡፡

የአህጉሪቱን የኃይል አቅርቦት ለመፍታት ካስፈለገ የአህጉሪቱ መሪዎችና አጋር ድርጅቶች በቀላል ወጪ ሊተገበሩ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ እንዲያውሉ የአፍሪካ ልማት ባንክና የቀድሞው የተመድ ዋና ጸሃፊ ኮፊ አናን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በውይይቱ ላይ እንደተገለጸው የአህጉሪቱን የሃይል አቅርቦት ለማሟላት በማዕከላዊ የሃይል ስርጭት ውስጥ በሚገቡና በማዕከላዊ የሃይል ስርጭት ውስጥ የማይገቡ የሃይል አቅርቦት ዘዴዎችን መጠቀም አስፈላጊ ነው ተብሏል፡፡

በአፍሪካ 645 ሚሊዮን ህዝብ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት የላቸውም፤ ይህም ደግሞ አህጉሪቱ ከፍተኛ የሃይል አቅርቦት እጥረት እንዳለባት ያሳያል ነው ያሉት የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አኪንዉሚ አዴሲና፡፡

እንደ አኪንዉሚ አዴሲና ገለጻ አህጉሪቱ ከፈተኛ የሆነ የጸሃይ ሃይል፤ ሃይድሮ ፓወር፤ የንፋስ ሃይል፤ ጂኦተርማልና የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ስላላት አማራጭ የሃይል አቅርቦት ይኖራታል፡፡

ባንኩ አህጉሪቱ የምጣኔ ሃብት እድገት የሃይል አቅርቦት ወሳኝ እንደሆነ በመገንዘቡ ለዚሁ አላማ ባንኩ 12 ቢሊዮን ዶላር ለመጪዎቹ አምስት አመታት መመደቡን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ ከአጋር ድርጅቶች በማሰባሰብ እንዲያገኙ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

በማዕከላዊ የሃይል ስርጭት ውስጥ የማይገቡ የሃይል አቅርቦት ዘዴዎች ወጪ ቆጣቢና ተግባራዊ ለማድረግም ቀላል በመሆናቸው የአፍሪካ መንግስታት ትኩረት ቢሰጡበት የተሻለ ነው ያሉት ደግሞ የቀድሞው የተመድ ዋና ጸሃፊ ኮፊ አናን ናቸው፡፡

ከዚህ ቀደም ሲሰራበት የነበረው የሃይል አቅርቦት እምብዛም ውጤታማ ባለመሆኑ ወጪ ቆጣቢና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን መከተል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ምንጭ፡- ኦል አፍሪካ