የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት ከ8 በመቶ በታች ሆኖ የቆየው መንግስት በዘረጋው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ስርዓት ነው ፡‑ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ

መጋቢት 07፡2009

የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት ከ8 በመቶ በታች ሆኖ የቆየው መንግስት በዘረጋው ጠንካራ የገንዘብ ፖሊሲ ስርዓት መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ለምክር ቤታቸው ባቀረቡት የግማሽ ዓመት ሪፖርት የተለያ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ዳሰዋል፡፡

የዋጋ ግሽበቱ በነጠላ አሀዝ ተወስኖ እንዲቆይ መንግስት እየተገበራቸው ያሉ የገንዘብ ፖሊሲዎች ውጤት  መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ፣የነዳጅና የብረት ዋጋ በአለም ገበያ የተረጋጋ ሆኖ መቆየቱን ፋይዳው የጎላ ነበር ብለዋል፡፡

በተይም የወለድ ምጣኔውን ስርዓት እንዲይዝ መደረጉ የአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ እንዲረጋጋም አስችሎታል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም እንዳሉት መንግስት ከብሄራዊ ባንክ የተበደረው 12 ቢሊዮን ብር ከዕቅዱ ጋር የተጣጣመ በመሆኑ የተረጋጋ የኢኮኖሚ ሂደት እንዲኖር አስችሏል፡፡

የአገሪቱ አጠቃላይ እድገት በ2008 ዓ.ም 11 በመቶ ይሆናል ተብሎ የተተነበየ ቢሆንም ድርቁ በግብርናው ላይ ባስከተለው አሉታዊ ተፅእኖ ምክንያት 8 በመቶ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የግብርናው ዘርፍ ወትሮ 7 በመቶ እድገት ያሳይ የነበረው፣ በኤሊኖ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ወደ 2.5 በመቶ ማሽቆልቆሉንም ጠቅላይ ሚስትሩ  አስረድተዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጡ ተፅእኖ እንዳለም ሆኖ ግን በአገር ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መቻሉንም አስምረውበታል፤ ይህም የአገሪቱ ኢኮኖሚ  በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ እንደሆነ ብለዋል ጠቅላይ ሚስትሩ በሪፖርታቸው፡፡

ይሁንጂ በተለያዩ አካባቢዎች ዘንድሮም እንደ አዲስ በተከሰተው  ድርቅ  5.6 ሚሊዮን ህዝብ የእለት ደራሽ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተናገረዋል፡፡

በእርዳታ ድርጅቶች ጋር በመሆን ለድርቁ ተጠቂዎች ከ948 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ የድርቁን ተፅእኖ ለመቋቋም ክልሎች ከበጀታቸው እያደረጉ ካለው ድጋፍ ባሻገር የፌደራል መንግስት የ1 ቢሊዮን ብር በጀት መድቦ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ከመላ አገሪቱ 5 ሚሊዮን ስራ አጥ ወጣቶች መለየታቸውን በሪፖርታቸው ያቀረቡት ጠቅላይ ሚንስትሩ፡ በቀጣይ በተለያዩ አመራጮች ወደ ስራ የሚገቡበት ሂደት እየተመቻቸ ነው ብለዋል፡፡

በሪፖርቱ እንደተገለፀው የፌደራል መንግስት የገቢ አሰባሰብ መጠን ዘንድሮ የ12.2 በመቶ እድገት ማሳየቱንና የአገሪቱ የእዳ ጫና ወደ መካከለኛ ደረጃ ዝቅ ማለቱም ተመልከቷል፡፡በአንፃሩ የወጪ ምርቶች ገበያ መቀዛቀዝ ተናግረዋል፡፡በቀጣይ በብዛትና በስፋት የወጪ ምርቶችን ለአለም ገበያ በማቅረብ ክፈተቱ ለመሙላት እንደሚሰራ አመልከቷል፡፡

የግብርናና የኢንዱስትሪውን ትስስር ለማጠናከር በክልሎች 4 የግብርና ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን አልምቶ  ወደ ስራ ለመግባት እየተሰራ መሆኑንም ጠ/ሚ ኃይለማርያም ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር በመንግስት እየተገነቡ ያሉ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከክልሎችና ከግሉ ባለሃብት ጥረት ጋር ተዳምሮ የአኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲኖር መሰረት መጣሉንም ተናግረዋል፡፡

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ 75 በመቶ የሚሆነውን በጀት ከአገር ውስጥ ምንጭ ለማመንጨት ታቅዶ እየተሰራ በመሆኑ የበጀቱ ዋና አካል ደግሞ ከግብር የሚገኝ በመሆኑ፣ የግብር ሰብሳቢ መስሪያቤቶችን አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ከምክር ቤቱ አባት ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የግብር ህግንም ጠንከር ባለ መልኩ የማስከበር ስራም በማሰኬድ በእቅድ ዘመኑ መጨረሻ የግብር አሰባሰብ ምጠኔውን 17 በመቶ ለማድረስ የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ኦዲትን አስመልክቶም የማጭበርበር ምልክት የታየበት የተመረመረ የመንግስት ተቋም ኦዲት ውጤይ በቀጥታ ለፌደራል መርማሪ ቢሮ ቀርቦ ተጨባጭ ህጋዊ እርምጃ ለማሶሰድ በሚያስችል መልኩ ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡

በናትናኤል ፀጋዬ