የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድና ሁለት የስኳር ፋብሪካዎች በተያዘላቸው ጊዜ ወደ ስራ ሊገቡ አልቻሉም

መጋቢት 07 ፣2009

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ ምርት ባለመጀመሩ በአስራ ሰባት ሺ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ የአገዳ ግብአት ብክነት እየደረሰበት ነው፡፡ በአንጻሩ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት የማሽን ሙከራ ጀምሯል፡፡

ነገር ግን ሁለቱም ፋብሪካዎች የሙከራ የስኳር ምርት ይጀምራሉ በተባለበት ጊዜ አልጀመሩም፡፡

የኦሞ  ኩራዝ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካም ግንባታ ስድስት ዓመት ቢያስቆጥርም ይጠናቀቃል በተባለለት ጊዜ በ2005 መጠናቀቅ እልቻለም፡፡

ግንባታውን የሚያከናውነው የኢፊዲሪ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን  በጥር ወር 2009 መጨረሻ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ተጠብቆ የነበር  ቢሆንም ገና ከ3ወር በኋላ ነው የሙከራ የስኳር ምርት ይጀምራል የተባለው፡፡

ፋብሪካው በተለያየ ወቅት ለ10 ጊዜ ያህል በዚህ ጊዜ ስራ ይጀምራል እየተባለ ቃል ሲገባለት እንደነበር  በስፍራው የሚገኘው የኢቢሲ ሪፖርተር ማረጋገጥ ችያለሁ ይላል፡፡

የዚህ ፋብሪካ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ ምርት ባለመጀመሩ በአስራ ሰባት ሺ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ የአገዳ ግብአት ብክነት እየደረሰበት መሆኑንም ዘጋቢው ባደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡   ይሁን እንጂ የኢቢሲ የጋዜጠኞች ቡድን ወደ ፋብሪካው ገብቶ እንዲጎበኝ በኮንትራክተሩ  የኢፊዲሪ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሳይፈቀድለት ቀርቷል፡፡

ሌላኛው በቻይናው ኮምፕላስ ኩባንያ ከ2007 ጀምሮ እየተገነባ ያለው የኦሞ ቁጥር 2 የስኳር ፋብሪካ ግንባታው እንዲጠናቀቅ የታሰበው በዚህ አመት በህዳር ወር ላይ ነበር ፡፡

ነገርግን የ3 ወራት መራዘሚያ ተደርጎለት በየካቲት ወር አጋማሽ የሙከራ የስኳር ምርት ይጀምራል ተብሎ ነበር፤ ይህም አልተጀመረም᎓᎓

የመሳሪያዎች ሙከራ ቢጀመርም የአገዳ መፍጨት ስራ ግን እስካሁን አልጀመረም፡፡

አቶ አለም ከበደ በስኳር ኮርፖሬሽን የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 የፋብሪካ ኦፔሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ "የፊኒሽንግ ስራ በተባለው ጊዜ ነው የተከናወነው ፤ በመሃል የኮሚሽኒንግ ጊዜ የሚያጋጥሙ የቴክኒክ  ችግሮች አሉ ፤ ለነሱ መፍትሄ እየተሰጠ ነው፡፡ የሙከራ የስኳር ምርት ጅማሮውንም ለአንድ ሳምንት አራዝመነዋል" ብለዋል፡፡

የፋብሪካው  ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ግርሻ ፋብሪካው በቅርብ ቀናት ውስጥ ስኳር ማምረት እንደሚጀምርም ለኢቢሲ ተናግረዋል᎓᎓

ሪፖርተር ፡‑ ተዓምርአየሁ ወንድም አገኝ (ከኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት )