ህብረቱ በአፍሪካ የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል አገራት ተቀራርበው እንዲሰሩ ጥሪ አቀረበ

መጋቢት 8፡2009

የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቱ የተከሰተውን ድርቅ እና ረሃብ ለመከላከል አባል አገራቱ ይበልጥ ተቀራርበው በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቀረበ፡፡  

አዲስ የተመረጡት የህብረቱ ሊቀመንበር ሞሳ ፋቂ ማሃማት በአፍሪካ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ እና ረሀብ ሊያደርስ የሚችለው ሰብዓዊ ጉዳት እጅግ እንዳሳሰባቸው ተገልጿል፡፡

ሊቀመንበሩ የህብረቱ አባል አገራት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ድንበራቸውን ክፍት በማድረግና እርዳታ በመስጠት አጋርነታቸውን ላሳዩ አገራት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የህብረቱ አጋሮች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት በአህጉሪቱ የተከሰተው አደጋ ወደ አሰቃቂ እልቂት ከመቀየሩ አስቀድሞ አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡ 

ከፍተኛየድንገተኛ ምግብ ዋስትና አደጋ በአፍሪካ መከሰቱንም የህብረቱ ፓን አፍሪካ ክንፍ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል፡፡

በደቡብ ሱዳን አንዳንድ አካባቢዎች ያለው አለመረጋጋትና ግጭት ድርቁን ወደ ረሀብ በመቀየሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ጎረቤት አገሮች መሰደድ መጀመራቸውንም ነው መግለጫው የሚያመለክተው፡፡

በተያያዘ ዜና በሰሜን ኬንያ አካባቢ ለተከሰተው ድርቅ የተባበሩት መንግስታት 166 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ምንጭ፡-  ሽንዋ እና ቢቢሲ