ጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም መቆጣጠር እንዳልተቻለ ተገለጸ

ሰኔ 5፣2009

የዛሬ አምስት አመት በ2004 ዓ.ም በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን እንቦጭ የተባለ አረም ለማስወገድ በየአመቱ አርሶ አደሩ ቢያርምም ማስወገድ እንዳልተቻለ ተገለጸ፡፡

አረሙን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ሥራ የሚያስተባረው የአማራ ክልል ደን፣ የዱር እንስሳትና አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከባህርዳና የጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የተለያዩ ጥናቶች እየተካሄዱ ነው ቢልም መፍትሄ አልተገኘም፡፡

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሥነ-ምዳር ተመራማሪው ዶክተር አያሌው ወንዴ እንደሚሉት ግን የእንቦጭ አረም አሳሳቢነት በጣና ሐይቅ ላይ ብቻ የሚወሰን አይደለም፤ይልቁንም እስከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና የታችኞቹ የዓባይ ተፋሰስ ሐገራትንም ይጨምራል፡፡

ዶክተር አያሌው ይህን አሳሳቢ ጉዳይ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መፍትሔ በማፈላለጉ ላይ ረጅም ርቀት አልተጓዘም ብለዋል ፡፡

በአማራ ክልል የሚገኙ ሰባት ዩኒቨርስቲዎችም እንቦጭን ለመቆጣጠር ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ የተቋቋመ ፎረም ቢኖርም ብዙም አልተሰራበትም ነው ያሉት፡፡

የአማራ ክልል ደን፣ የዱር እንስሳትና አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ ግን መንግስት ትኩረት አልሰጠም በሚለው ጉዳይ ላይ አይስማሙም፡፡ ይልቁንም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን በዘላቂነት አረሙን ለማስወገድ በሚቻልባው ጉዳዮች ላይ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ እንቦጭ አረሙን የሚመገቡ ጢንዚዛዎችን የማራባት ሙከራ እየተካሄደ ነው፤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲም አረሙን ከሐይቁ ላይ እያጨደ የሚፈጭ ጀልባ ስርተው በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሌሎች ምርምሮች እየተካሄዱ ቢሆንም አረሙን ለመቆጣጠር በተጨባጭ ወደስራ የገባ መፍትሄ አለመኖሩን ግን ገልጸዋል፡፡

አረሙ በፍጥነት የሚራባና ዘሩ ለረጅም አመታት በመሬት ውስጥ የሚቆይ በመሆኑ እርጥበት ሲያኝ እንደገና እየበቀለ የማስወገድ ሂደቱን ፈታኝ እንዳደረገው ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ይህም ሆኖ አረሙን ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድ የቴክኖሎጂም ሆነ የእውቀት ችግር ገጥሞናል ያሉት ዳይሬክተሩ በጊዜያዊነት ግን አረሙን በሰው ሃይል እንዲታረም እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋ፡፡

ሪፖርተር፡- ጌቱ ላቀው