የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናትን ለመርዳት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

ሰኔ 8፤2009

ከጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት ነፃ የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ፡፡

ከጥር ወር ጀምሮ በጎዳና ላይ የሚገኙ ህፃናትን በመደገፍና በተለያዩ ፕሮግራሞች ሲከበር የቆየው 26ኛው የአፍሪካ ህፃናት ቀን ሰኔ 9 ቀን 2009 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ ይጠቃለላል፡፡    

በዓሉን አስመልክቶ በአገር አቀፍ ደረጃ በ60 ከተሞች በተደረገ ጥናትም ከ12 ሺህ 6 መቶ በላይ ኑሯቸውን በጎዳና ያደረጉ ህፃናት ተለይተው ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን የህፃናት መብትና ደህንነት የማስጠበቅ ዳይሬክቶሬት ዳይሪክተር አቶ ክብሪ ሀይሌ ገልፀዋል፡፡   

እንደ ዳይሪክተሩ ገለፃ በጥናቱ ከተለዩት ህፃናት መካከል ወላጅ ያላቸው ወደ ወላጆቻቸው እንዲቀላቀሉ፤ ወላጅ የሌላቸው ህፃናት ደግሞ ወደ ተለያዩ የድጋፍ ሰጪ ማእከላት እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

በተጨማሪም ከ14 ዓመት በላይ የሆኑ ህፃናት የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎችና ስራ እንዲያገኙ የሚያስችል ድጋፍ ማግኘታቸውን ነው አቶ ክብሪ የገለፁት፡፡

26ኛው የአፍሪካ ህፃናት ቀን "ባስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህፃናትን ለመደገፍ የሁሉም አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው" በሚል መሪ ቃል በፓናል ውይይቶች፣ በጥያቄና መልስ ውድድሮች እንዲሁም በተለያዩ የንቅናቄ ስራዎች በመከበር ላይ ነው፡፡

በናትናኤል ፀጋዬ