ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች በቂ ትኩረት አልተሰጠም፦ጤና ጥበቃ

ሰኔ 8፤2009

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ በቂ ትኩረት አለመሰጠቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

በአሁን ወቅት የሀገሪቱ እድገትን ተከትሎ በከተሞች መስፋፋትና የዜጎች የአኗኗር ዘይቤ በመቀየሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በፍጥነት እየተስፋፉ ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህም በሽታዎች መካከል ስኳር፣ ደም ግፊት፤ ካንሰር፣ አስም፣ የጉሮሮ ህመምን ተከትሎ የሚከሰት የልብ በሽታና የአህምሮ ጤና በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ሙሴ ገብረሚካኤል ለኢቢሲ እንደገለፁት በአመዛኙ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በፍጥነት የተስፋፉትበቂ የሆነ ጥናት ባለመደረጉ ነው፡፡

በሽታዎቹን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ክልሎች በተለይም ታዳጊ ክልሎች በቂ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ አይደሉም ብለዋል፡፡

በቀጣይ የበሽታዎቹን መስፋፋት ለመግታትም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ከመከወን ባለፈ የበሽታዎቹን ህክምና አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት ለጤና ባለሞያዎች የተለያዮ ስልጠናዎች ይሰጣል ብለዋል፡፡

የእድሜ መጨመር፣ ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ባህል መከተል፣ በየጊዜው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያለማድረግ፣ የአየር ብክለት መጨመር ሲጋራ ማጨስ፣ ጫት መቃምና የአልኮል መጠጥ በብዛት መጠቀም ሌላኛዎቹ የበሽታዎቹ ተጋላጭነትን የሚጭምሩ መንስኤዎች ናቸው፡፡

ለአብነትም በሀገሪቱ የካንሰር በሽታን ስርጭት ብቻ ብንመለከት በየዓመቱ 120 ሺህ 500 አዋቂዎች እንዲሁም 6 ሺህ ህፃናት ልጆች በበሽታው እንደሚያዙ ባለሙያው ገልጸዋል፡፡

በሰለሞን አብርሃ